አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገራት የልማት ጉዞ ጠንካራ ተቋማትን፣ የሕዝብ ተሳትፎንና የዴሞክራሲ ባህልን መገንባት የሚጠይቅ እንደመሆኑ ኢትዮጵያ ያከናወነችው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የእድገት ጉዞዋ ጉልህ ምዕራፍ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት ብትሆንም፤ በአንጻሩ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድና በሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ረገድ ለበርካታ ዓመታት ረጅም ጉዞ የሚቀራት ሀገር ሆና ቆይታለች፡፡
ዘንድሮ የተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ግን ይህን መንገድ የቀየረ፤ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ለዴሞክራሲያዊት ሀገር ግንባታ ያላቸውን መሻት ያሳዩበት ሆኖ አልፏል፡፡
ዜጎች ህገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው ብርድና ጨለማው ሳይበግራቸው፤ ድካም ሳይረታቸው ይበጀናል ላሉት ቀድመው በመውጣት ድምጽ በመስጠት ስልጡንነታቸውን አሳይተዋል፡፡
የምርጫው ሂደት በተለይም በመራጮችና እጩዎች ምዝገባ ሂደት በዲጂታል ሥርዓት የታገዘ ከመሆኑ ባሻገር ደህነቱ በተጠበቀ መንገድ የተከናወነ ነበር፤ በዚህም ለዲጂታል ኢትዮጵያ አዲስ ታሪክ ካስመዘገቡ ሁነቶች አንዱ ሆኗል፡፡
ምርጫው በስኬት የተጠናቀቀው ምርጫውን ዋጋ ለማሳጣትና ሕዝቡ ድምፁን እንዳይሰጥ አሳሳች መልዕክቶችን ከማሰራጨት ባለፈ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን ለማወክ በተደረጉ የጥፋት ሙከራዎች ውስጥ አልፎ መሆኑ የሕዝቡን ጽናት ያጎላዋል፡፡
የሚበጀውን በውል የተረዳው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን አላስፈላጊ ድምጾችን ወደ ጎን በማለት በነቂስ ወጥቶ ድምጽ ሰጥቷል፡፡
ዜጎች ዛሬ ላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ለነገው ትውልድ መሰረት መሆናቸውን በማመን በእጃቸው በያዙት ካርድ ለትውልድ የምትሻገር ሀገር ይገነባል ያሉትን መርጠዋል፤ ውጤቱንም አክብረው ተቀብለዋል፡፡
ሀገር በጠመንጃና በጦርነት ሳይሆን በሰላማዊ ምርጫ እንዲሁም ሀሳብ በሚሸጥበት በምክክር ሂደት እንደምትገነባ በመገንዘብ ዜጎች ይህንኑ አድርገዋል፡፡
ከተለያዩ ሀገራት ምርጫውን ለመታዘብ የመጡ ልዑካን ጭምር በሕዝቡ ንቁ ተሳትፎ ተደንቀው፤ ኢትዮጵያ እና ሕዝቧ ሊኮሩ ይገባል ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ይህ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ የባለቤትነት ስሜትን በመያዝ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን፤ ሀሳባቸው ዋጋ እንዳለው ማመናቸውንና ከምንም በላይ ለለውጥ ያላቸውን ተነሳሽነት የሚያሳይ ነው፡፡
በተጨማሪም ሕዝቡ በገለልተኛ ተቋማት ላይ ያለውን እምነት ያጠናከረበት፣ ተቋማትም የተጣለባቸውን እምነት በአግባቡ መወጣት እንደሚችሉ ያሳዩበት አጋጣሚ ሆኗል፡፡
ይህም ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን የልማትና ሀገር ግንባታ ስራዎች በተገቢው አቅጣጫ ለማስኬድ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡
በመሆኑም የምርጫው ሂደት ሕዝቡ በድምጹ ከመረጠው መንግሥት ጋር የሀገር ግንባታ ውል ያሰረበትና ለልጆቹ የሚያወርሳትን ኢትዮጵያን የከተበበት ሁነት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ሀሳብ የችግር መፍቻ የመጀመሪያ መንገድ በመሆኑ ኢትየጵያ ያሸነፈችው ዛሬ ሳይሆን፤ ጦርነት አልበጀንም ብላ ዴሞክራሲያዊ ምርጫና ምክክርን ስትወጥን ነው፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ እና ዜጎቿ አሸናፊነታቸውን አሳይተዋል፤ በምርጫው እና በምክክር ሂደቱ የተገለጡት መልኮችም የዜጎች ዝማኔ ማሳያ ናቸው፡፡
በቤተልሔም ግርማ