የሀገር ውስጥ ዜና

የታሪክ፣ የፅናትና የሀገር ሕልውና ዘብ

By Hailemaryam Tegegn

August 26, 2026

“ከመሞት በላይ ለመሞት” የተገባ ቃል፣ ሺህ ጊዜ ደም ቢፈስ በመስዋዕትነት ሀገር የማስቀጠል ኪዳን…”

ይህ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መዝሙር ላይ የተወሰደ ስንኝ፣ የቃላት ውበት ብቻ ሳይሆን ተቋሙ ለሀገር ሕልውናና ለህዝቦች ደህንነት ሲል የገባውን የማይናወጥ የመስዋዕትነት ቃል ኪዳን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሕያው ምስክር ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር የጀግንነትና የአርበኝነት ውርስ ሲሆን፣ ይህ ውርስ በአበው ደም የተመሰረተና በላብ የፀና ነው።

ዛሬም ድረስ በየዓውደ ውጊያው ላይ በተግባር የሚገለጥ ሕያው ቃል ኪዳን ነው። ሠራዊቱ ለሀገሩ ያለውን ፍቅር በቃላት ብቻ ሳይሆን በህይወት መስዋዕትነት የሚገልጽ፣ ለህገ መንግስቱና ለህዝቦቹ አንድነት ዘብ የቆመ ኃይል ነው።

የኢትዮጵያ ሠራዊት ጥንካሬ የሚመነጨው ካለፈው ታሪክ ብቻ ሳይሆን፣ ያንን ታሪክ ወደ አዲስ ትውልድ በማሸጋገር ከማጠናከር ችሎታውም ነው።

እያንዳንዱ ወታደር የቀደምት ኢትዮጵያውያንን የነፃነት ተጋድሎ እንደ አደራ ተቀብሎ፣ በራሱ ዘመን ላይ አዲስ የጀግንነት ታሪክ ለመጻፍ ቁርጠኛ ሆኗል። ፈተናዎች እንደ ማዕበል ቢነሱም፣ ሠራዊቱ ከውስጡ በሚመነጭ ጥንካሬ ተጋፍጦ የማለፍ ልምድ አዳብሯል።

የመከላከያ ሠራዊቱ ጥንካሬ ምንጩ ራሱ ህዝቡ ነው። ከተለያዩ የኢትዮጵያ ማዕዘናት የተውጣጡ ወታደሮች፣ በጋራ እሴቶች ላይ ተመስርተው አንድ ላይ ይቆማሉ፤ ግርማቸው ጠላትን ያስፈራል፣ ይርዳልም።

ሰላምና ልማት የጋራ ግባቸው፣ እኩልነትና መከባበር የአብሮነታቸው መሠረት ነው። ይህ የተለያዩ ማንነቶችን በአንድ ዓላማ ስር የሚያሰባስብ አቅም፣ ለሠራዊቱ ልዩ የሆነ ውስጣዊ ጥንካሬን ይሰጠዋል።

ሠራዊቱ ለጠላቱ የማይበገር ኃይል ሆኖ የቆመው በአካላዊ ብቃት ብቻ ሳይሆን፣ በውስጡ ባለው የማይናወጥ ወኔ ጭምር ነው። ይህ ወኔ ከቅርበት ብቻ ሳይሆን ከርቀትም እየተሰማ ጠላትን የሚያሸማቅቅ፣ ማንኛውንም መሰናክል የመስበር አቅም ያለው ነው።

ለሀገር ክብር ሲባል የሚከፈል ዋጋ ምንም ያህል ከባድ ቢሆን፣ ሠራዊቱ ወደ ኋላ የማይል ቁርጠኝነትን ያሳያል።የሠራዊቱ አባላት ለሀገራቸው የገቡትን ቃል ኪዳን ከግል ህይወታቸው በላይ የሚያስቀምጡት ነው።

ኢትዮጵያ በክብር እንድትኖርና ስሟ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲከበር፣ የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን በተግባር ያሳያሉ። ይህ ቁርጠኝነት “ከመሞት በላይ ለመሞት” የተገባ ቃል ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ጥልቅ የሀገር ፍቅር መገለጫ ነው።ይህ የፅናትና የቁርጠኝነት እሴት በንድፈ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ ስራ ላይ የተመሰረተ ነው።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ለ45ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን የጽናት ኮርስ መሠረታዊ ኮማንዶዎች ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ የአየር ወለድና ኮማንዶ ኃይል በአካል ብቃቱ፣ በጽናቱና በከፍተኛ ወታደራዊ እውቀቱ የውጊያ አቅጣጫ ቀያሪ ኃይል እንደሆነ አብራርተዋል። ይህ ወትሮ ዝግጁነትና ብቃት የሁሉም የመከላከያ ሠራዊት ምልክት ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከትናንት ወደ ዛሬ፣ ከዛሬም ወደ ነገ የሚሸጋገር የፅናት ተምሳሌት ነው። በአንድነት የተገነባ፣ ለህገ መንግስቱ ታማኝ፣ እናም ለሀገር ክብር ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ የሆነ ኃይል ነው።

ይህ ትውልድ የተረከበውን የአርበኝነት አደራ በብቃት እየተወጣ፣ ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር እንድትኖር የማይናወጥ ዘብ ሆኖ ቀጥሏል።

በአፈወርቅ እያዩ