አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብን በተያዘው ጊዜ ገደብ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው አለ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል፡፡
የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ መብራቱ ተሾመ (ኢ/ር) እንዳሉት÷ አሁን ላይ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድቡ አጠቃላይ አፈጻጸም ከ77 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡
ግድቡ 201 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ÷ የኃይል ማመንጫ ቤቱ የቁፋሮ ሥራ እንዲሁም የሲቪል ሥራው የመጀመሪያ ደረጃ የኮንክሪት ሙሌት ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ተናግረዋል።
6 ነጥብ 4 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ የአፈር ቁፋሮ በማካሄድ አጠቃላይ ግድቡ ከሚፈልገው 7 ነጥብ 72 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ የኮንክሪት ሙሌት ውስጥ 81 ነጥብ 2 በመቶ የኮንክሪት ሙሌት ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል።
የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራውን በታቀደው ጊዜ ለማጠናቀቅ ዕቃዎቹ በበርካታ ፋብሪካዎች እንዲመረቱ መደረጉን አመልክተዋል፡፡
ተቋሙ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ በራሱ በመሸፈን ግንባታው እየተፋጠነ እንደሚገኝ ነው ሥራ አስኪያጁ ያስገነዘቡት፡፡
የግድብ ግንባታውን በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ በማጠናቀቅ በጥቅምት 2021 ዓ.ም የመጀመሪያውን ተርባይን ወደ ኦፕሬሽን ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የፕሮጀክቱን ግንባታ እስከ ግንቦት 2021 ዓ.ም ድረስ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ታቅዶ በቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል፡፡