የሀገር ውስጥ ዜና

መሶብ ለተሳለጠ እና ለውጤታማ አገልግሎት አሰጣጥ

By tigist gizachew

August 26, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ ቴክኖሎጂን እንደ ቁልፍ መሳሪያ በመጠቀም እመርታዊ ለውጦችን እያመጣ ይገኛል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የዜጎችን እንግልት በመቀነስና የመንግሥት አሰራርን በማዘመን ረገድ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው።

ማዕከሉ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አሰራርን በአንድ ቦታ ላይ በማቅረብ ዜጎች የሚፈልጓቸውን አገልግሎቶች በአንድ ቦታ ፈጣን፣ ጥራት ያለውና ምቹ በሆነ ሁኔታ እንዲያገኙ አድርጓል።

ይህም የመንግሥትን አገልግሎት አሰጣጥ ከማሳለጡ ባለፈ፤ አጠቃላይ አሰራሩን ግልጽ በማድረግ ብልሹ አሰራርን በከፍተኛ ሁኔታ መከላከል ችሏል፡፡

የፌዴራል መሶብ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ አለማየሁ እንደገለጹት፤ የመንግሥት የአገልግሎት አሰጣጥ በሂደት መቀየርና መሻሻል የሚገባው ትልቅ ክፍተት በመሆኑ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት መቋቋሙን ገልጸዋል።

አገልግሎቶቹን ዲጂታላይዝድ ከማድረግ ባሻገር ተበታትነው የሚገኙ የመንግሥት አገልግሎቶችን ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት የተሳለጠ እና ውጤታማ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

ማዕከሉ የተበታተኑ የመንግሥት አገልግሎቶችን አቀናጅቶ ለዜጎች በአንድ ማዕከል መስጠት ሲሆን ይህም ስኬታማ ነው፡፡

አገልግሎቶቹን በማቀናጀት ብቻ ሳይወሰን ለዜጎች የሚሰጠው አገልግሎት እርካታን የሚያመጣ እንዲሆን ማድረግ ሌላው የማዕከሉ ዋና ዓላማ ሲሆን፤ በዚህ ረገድም ውጤታማ ሆኗል፡፡

የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ110 በላይ ማዕከላት መድረሱንና እስካሁን ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ተገልጋዮች አገልግሎት መስጠት ችሏል፡፡

የዜጎችን የአገልግሎት ፍላጎት በፍጥነትና በቅልጥፍና ለማሟላት የተለያዩ የአገልግሎት ሞዳሊቲዎችን ተግባራዊ እያደረገ ነው፡፡

በአካል ወደ ማዕከሉ መምጣት የማይችሉ ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ የሞባይልና የተንቀሳቃሽ አገልግሎት ተጀምሯል፡፡

በዚህም በፌደራል ደረጃ ሁለት እና በአዲስ አበባ ከተማ አንድ በድምሩ ሦስት ተንቀሳቃሽ የመሶብ አገልግሎቶች ሥራ ጀምረዋል፡፡

በተጨማሪ የኦንላይን አገልግሎትና የአፕሊኬሽን ሞዳሊቲዎችን በመጠቀም አገልግሎቶችን እያቀረቡ ነው፡