አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) በቀጣናው ሰላም እና ደህንነትን በማረጋገጥ ረገድ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሞሐመድ አሊ ዩሱፍ ከኢጋድ ዋና ፀሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ሁለቱ ወገኖች የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን ሰላም እና ደህነት ማረጋገጥ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት ÷ በሱዳን ሰላም ለማስፈን ጥረት ከሚያደርገው የሱዳን የሰላም ተልዕኮ ጋር የነበራቸውን ቆይታ አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል፡፡
በውይይቱ በሱዳን ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ኢጋድ እና የአፍሪካ ህብረት ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የህብረቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
በሚኪያስ አየለ