አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመደመር መንግሥት እሳቤ የሚከናወነው ሰው ተኮር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማሕበረሰቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው አሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፡፡
በክልሉ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለአቅመ ደካሞችና አነስተኛ ገቢ ላላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ልጆች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።
አቶ ኦርዲን በድሪ በዚህ ወቅት÷ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዋና መርህ «ከእኔ በፊት ለኛ» የሚል እና አንዳችን ለሌላችን ቆመን ሁላችንንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት መዘርጋት ነው ብለዋል፡፡
የአገልግሎቱ ዋና ዓላማ ሰው ተኮር በሆነ መንገድ የኢኮኖሚ ፍትህ ማረጋገጥ እና ማህበረሰቡን እኩል ተጠቃሚ ማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረውን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሕይወት መርሐችን እና የዕለት ተዕለት ተግባራችን ልናደርገው ይገባል ነው ያሉት፡፡
በጎ ፈቃደኝነት የውስጥ እርካታን የሚያስገኝ እና የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ ከክረምት ባለፈ በበጋ ወራትም ተጠናክሮ ባህል ሆኖ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
የተደረገው ድጋፍ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ በማሟላት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ እና ለተሻለ ውጤት እንዲበቁ እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል በክልሉ በ12ኛ ክፍል ለተመዘገበው ስኬት መምህራንን፣ ወላጆችንና ተማሪዎችን አመስግነው÷ በቀጣይም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የጋራ ርብርብ ማድረግ ይገባል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡