የሀገር ውስጥ ዜና

ካልተነካ እምቅ ሃብትነት ወደ ኢኮኖሚ ዋና ሞተርነት

By Melaku Gedif

August 28, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በጉያዋ በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶችን አቅፋ የያዘች ቢሆንም፣ ላለፉት አሥርት ዓመታት ይህ እምቅ ሀብት በአፈር ተሸፍኖና በልማዳዊ አሠራር ተቀፍድዶ ቆይቷል።

እንደ ወርቅ፣ ታንታለም፣ ፖታሽ፣ ሊቲዬም፣ የከበሩ ድንጋዮችና የድንጋይ ከሰል ያሉ ስትራቴጂካዊ ማዕድናት በበቂ ሁኔታ ጥቅም ላይ ባለመዋላቸው፣ ዘርፉ ለሀገሪቱ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ያበረክት የነበረው አስተዋጽኦ ከ0 ነጥብ 8 በመቶ የሚበልጥ አልነበረም።

ይሁን እንጂ ባለፉት አምስት ዓመታት በተተገበሩት ሀገር በቀል የኢኮኖሚና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፣ ዘርፉ ከኮንትሮባንድና ከቀደሙ ማነቆዎች በመውጣት የሀገሪቱ አምስት ቁልፍ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ ለመሆን በቅቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ ጊዜያት እንዳነሱት፡ “ማዕድን የኢትዮጵያ የወደፊት የብልጽግና መሠረት ነው። ሀገራችን ያለችበትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ እና የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ዘርፉን ማዘመን አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፤” በማለት የሰጡት ስትራቴጂካዊ ትኩረት ለውጡን አፋጥኖታል።

በዚህም በአምስት ዓመታት ውስጥ ዘርፉ ተጨባጭ የኢኮኖሚ አበርክቶዎች እንዲኖሩት አድርጓል። ለአብነት በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት ከማዕድን ኤክስፖርት ከ5 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማግኘት የተቻለው በዘርፉ ላይ የተሰሩ ስራዎች ውጤት ማሳያ ነው።

የማዕድን ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚያሳዩት÷ ይህ ገቢ ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር የ92 በመቶ የገቢ ዕድገት እና የ27 በመቶ የምርት መጠን ብልጫ አለው።

ከዚህ ውስጥ ደግሞ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የወርቅ ምርት ሲሆን÷ በኩባንያዎችና በባህላዊ አምራቾች ትብብር ዓመታዊ የወርቅ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

በ2017 በጀት ዓመት ብቻ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን ÷ ይህ በ2018 በጀት ዓመት ከፍ ብሎ 44 ቶን ወርቅ በማምረት 5 ነጥብ 65 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ አስገኝቷል።

ከተመረተው 44 ነጥብ 067 ቶን ወርቅ ውስጥ ደግሞ 40 ነጥብ 86 ቶን ያህሉ በባህላዊ ማዕድን አምራቾች የተመረተ ሲሆን÷ ቀሪው 3 ነጥብ 209 ቶን ወርቅ በኩባንያዎች የተመረተ ነው።

ይህም የሚያሳየው አሁንም ለወርቅ ምርት ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የባሕላዊ የወርቅ ምርት እንደሆነ እና የኩባንያዎች የምርት ድርሻ ላይ ይበልጥ መሰራት እንዳለበት ነው።

ለዚህም መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመታት የወርቅ ምርቱን መጠን ለማሳደግ እና የጥራት ደረጃውን ከፍ ለማድረግ ለበርካታ ሀገር በቀልና የውጭ ወርቅ አምራች ኩባንያዎች የከፍተኛና መካከለኛ ደረጃ የማምረትና የፍለጋ ፈቃድ ሰጥቷል። ይሁን እንጂ ፈቃድ ከተሰጣቸው አምራች ኩባንያዎች ውስጥ እስካሁን ወደ ሥራ የገቡት ጥቂቶቹ ናቸው።

መንግሥት ፍቃድ ወስደው በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሥራ ያልገቡ ኩባንያዎችን ወደ ሥራ ለማስገባትም ጥብቅ መመሪያ ያስቀመጠ ሲሆን÷ በቀጣዮቹ ዓመታት ሌሎቹ የወርቅ አምራች ኩባንያዎች ሥራቸውን እንደሚጀምሩ ይታመናል።

በተለይም በቀጣይ 2019 በጀት ዓመት ከዘርፉ 6 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት እቅድ መያዙን ተከትሎ እነዚህ ኩባንያዎች ሥራቸውን እንዲጀምሩ ይጠበቃል።

ከወርቅ ባለፈ የከበሩ ድንጋዮች፣ ታንታለም፣ የድንጋይ ከሰል፣ የሲሚንቶ ግብዓቶች እና የተፈጥሮ ጋዝ አሁን ላይ ለኢኮኖሚው አጋዥ እየሆኑ መጥተዋል።

በተለይም በድንጋይ ከሰል ምርት ላይ ብንመለከት ከዚህ ቀደም ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት እያስቻለ ይገኛል። ለምሳሌ በ2010 ዓ.ም 17 በመቶ የነበረው የሀገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ገበያ ድርሻ በ2017 ዓ.ም ወደ 75 በመቶ ከፍ ብሏል።

በዚህም የሲሚንቶ ዓመታዊ ምርት ባለፉት ዓመታት ከነበረበት 8 ሚሊየን ቶን እስከ 20 ሚሊየን ቶን ማደጉ ይታያል። ይህም እንደ ሴራሚክ፣ መስታወትና ብረት ካሉ የኢንዱስትሪ ማዕድናት ጋር ተዳምሮ የኮንስትራክሽንና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ በሀገር ውስጥ ግብዓት እንዲደገፍ አድርጓል።

በአጠቃላይ በማዕድን ዘርፉ ባለፉት አምስት ዓመታት መንግሥት ከግብርናው በመቀጠል ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንዲሆን አድርጎ በመቅረጹና ግዙፍ ኢንቨስትመንቶችን በመሳቡ፣ ለሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት ጀምሯል።

በተቀመጠው የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ መሠረትም የማዕድን ዘርፉ ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ገቢ (ጂዲፒ) ያለው ድርሻ 10 በመቶ እንዲሸፍን ግብ ተቀምጦ እየተሠራ ይገኛል።

ፈቃድ የወሰዱ ግዙፍ የወርቅ፣ የፖታሽና የሌሎች ማዕድናት ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ማምረት ሲሸጋገሩ ደግሞ ዘርፉ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ መዋቅር በመቀየር ረገድ ግንባር ቀደም ሚናውን እንደሚጫወት ይታመናል።

በታሪኩ ለገሰ