የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካን የኢኮኖሚ ውህደት ለማፋጠን የድንበር ላይ አሰራሮችን ማሳለጥ ይገባል – የአፍሪካ ሕብረት

By betelhem girma

August 28, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካን የኢኮኖሚ ውህደት ለማፋጠን የሀገራትን የድንበር ላይ አሰራሮችን የሚያሳልጥ ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል አለ የአፍሪካ ሕብረት።

በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን እና በዓለም ባንክ ተዘጋጅቶ “አፍሪካን ማቀናጀት፤ ከተበታተኑ ትስስሮች ወደ ኢኮኖሚያዊ ማዕከላት” የተሰኘ አዲስ አህጉራዊ የጥናት ሪፖርት ይፋ ሆኗል።

ሪፖርቱ የአፍሪካን ከቀረጥ ነፃ የንግድና የምርት ትስስር በማጠናከር፣ የአህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣናን በዘመናዊ መሠረተ ልማት በማስደገፍ የኢኮኖሚ ውህደቱን ማጠናከር እንደሚገባ አመላክቷል።

በሕብረቱ ኮሚሽን የኢኮኖሚ ልማት፣ ንግድ፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪና ማዕድን ኮሚሽነር ፍራንሲስካ ታቾፕ ቤሎቤ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት÷ አፍሪካ በተሰናሰለ አሠራርና መሠረተ ልማት የሚመራ የኢኮኖሚ ውህደትን ማሳለጥ ይኖርባታል።

ይህም የተበታተነውን የገበያና የግብይት ሥርዓት ውጤታማ በማድረግ አህጉሪቱን የጠንካራ ኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

የኢኮኖሚ ውህደቱ በሚፈረሙ ስምምነቶች ብቻ እንደማይሳካ የጠቆሙት ኮሚሽነሯ÷ ለዚህም የአባል ሀገራትን የድንበር መተላለፊያ፣ ጉምሩክ፣ ታሪፍና የዲጂታል ክፍያ እንቅፋቶችን ማስወገድ የሚያስችል ቀልጣፋ አሠራር መዘርጋት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

አሰራሩ ጥሬ ዕቃን ከመላክ የተላቀቀ የኢንዱስትሪ፣ የኃይልና የትራንስፖርት እሴት ሰንሰለት በማጎልበት የአጀንዳ 2063 ራዕይን ለማሳካት ያስችላል ብለዋል።

የዓለም ባንክ የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣናዊ ምክትል ፕሬዝዳንት ንዲያሜ ዲዮፕ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የተቀናጀ የመሠረተ ልማት አቅርቦት በአርሶ አደሩ፣ በኢንዱስትሪና በገበያ መካከል ዘላቂ ትስስር እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

ተቋሙ የንግድ እንቅፋቶችን በመቀነስና የድንበር ተሻጋሪ አሠራሮችን በማቃለል ለሚገነቡ መሠረተ ልማቶች ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።