የሀገር ውስጥ ዜና

የመስጠት ባህል፡ ኢትዮጵያውያን በጎነትን ሲለማመዱ

By Melaku Gedif

August 29, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጎነት በኢትዮጵያ ምድር አዲስ ነገር አይደለም።እናቶች ለጎረቤት ልጅ ወተት የሚያካፍሉበት፣ “እድር” እና “እቁብ” መሰል ማህበራዊ ተቋማት በሐዘንም በደስታም አብረው የቆሙበት ባህል ለዘመናት ኖሯል።

ያ ጥንታዊ የመተሳሰብ መንፈስ ግን ባለፉት ዓመታት አዲስ ቅርጽ እየያዘ፣ ከግለሰብ ወይም ከቤተሰብ ደረጃ ወጥቶ ወደ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ እየተሸጋገረ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ፣ በጎ ፈቃደኝነት ከግለሰብ ጥረት ወደ ተቋማዊ ልምድ የተሸጋገረበት መንገድ ግልጽ ሆኖ ይታያል።

የመደመር መንግሥት የሰራቸው ሥራዎች ለዚህ ምስክር ናቸው፡፡ “የአረንጓዴ ዐሻራ” መርሐ ግብር በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን በችግኝ ተከላ አሰልፎ ምድሪቱን ማልበስ ብቻ ሳይሆን፣ “የጋራ ስራ ለጋራ ውጤት” የሚል አዲስ ብሔራዊ ልማድ መስርቷል። እንደዚሁም የከተማ ውበት ስራዎች፣ የደም ልገሳ ዘመቻዎች እና ወጣቶች በራሳቸው ጊዜ ለማሕበረሰባቸው የሚያደርጓቸው የጽዳት እና የድጋፍ ስራዎች እየበዙ መጥተዋል።

ይህ ለውጥ ትርጉሙ ትልቅ ነው፤ ምክንያቱም ማህበራዊ ችግር በመንግሥት ብቻ ሳይሆን በዜጎች ትብብርም ሊፈታ እንደሚችል ስለሚያሳይ ነው።

የመንገድ ዳር ችግኝ ከመትከል እስከ የጎዳና ተዳዳሪዎችን መርዳት፣ ከትምህርት ቤት እድሳት እስከ የአረጋውያን ማዕከላት ድጋፍ ድረስ፣ ዜጎች ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን እና ገንዘባቸውን ለሌላው ሕይወት እያዋሉ ነው።

ይህ ደግሞ ድህነትን ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ መራራቅንም የሚፈታ መድሃኒት ነው፤ አብሮ የመስራት ተግባር ራሱ የመተማመንና የመቀራረብ ድልድይ ይሆናልና።

የበጎነት ያጠኑ ምሁራንም ተመሳሳይ ሀሳብ ያንፀባርቃሉ። አዳም ግራንት በተለያዩ ጽሑፎቹ እንደሚያስረዳው፣ ለሌላው የሚሰጡ ማህበረሰቦች በረጅም ጊዜ ውስጥ የበለጠ ጠንካራ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ትስስር ይገነባሉ፤ መስጠት የሚያዳክም ሳይሆን የሚያጠናክር ልማድ እንደሆነ ያሳያል።

ሮበርት ፑትናምም በበኩሉ በጻፋቸው ሥራዎች÷ ዜጎች በጋራ ተግባር ላይ በንቃት ሲሳተፉ የሚፈጠረው “ማህበራዊ ወረት” ለዴሞክራሲና ለልማት ወሳኝ መሠረት እንደሆነ ይገልጻል። እነዚህ ሀሳቦች የኢትዮጵያን ወቅታዊ ተሞክሮ ሲያገናኙት፣ የምናየው ነገር ግልጽ ነው፡

በጎ ፈቃደኝነት ወደ ባህል ሲያድግ፣ ሀገርን ከውስጥ የመገንባት ትልቁ መሳሪያ ይሆናል።በጎ ፈቃደኝነት ከቃል ወደ ተግባር፣ ከግለሰብ ወደ ማህበረሰብ እየተሸጋገረ መሆኑ የማይካድ እውነታ ነው።

እያንዳንዱ የተተከለ ችግኝ፣ እያንዳንዱ የተለገሰ የደም ጠብታ፣ እያንዳንዱ ያለምንም ክፍያ የተሰራ የጽዳት ስራ፣ ኢትዮጵያ ወደፊት ለምትገነባው ትውልድ የሚተላለፍ ውርስ ነው። መስጠት ሲለመድ ማሕበረሰብ ይጠነክራል፤ ማሕበረሰብ ሲጠነክር፣ ሀገር ትጠነክራለች።