ዓለምአቀፋዊ ዜና

ዛፍ ላይ በመውጣት ከአስከፊው የኔፓል ጎርፍ አደጋ ያመለጠው ታዳጊ

By Mikias Ayele

August 29, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2018 (ኤፍ ቢ ሲ) የ8 ዓመቱ ዞያል ጋሊ ዛፍ ላይ በመውጣት ራሱን ከአስከፊው የኔፓል ጎርፍ አደጋ ማትረፍ ችሏል፡፡

እንደ ወትሮው ዞያል ጋሊ እና ወንድሙ አደጋው ከመከሰቱ በፊት ብስክሌታቸውን እየነዱ ወደ ትምህርት ቤት በመሄድ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ሀገር አማን ብለው ወደ ትምህርት ገበታቸው ያቀኑት ወንድማማቾች ያልታሰበ ነገር ገጠማቸው፤ በዕለቱ አመሻሽ አካባቢ አስከፊው የኔፓል የጎርፍ አደጋ ተከሰተ፡፡

የተከሰተውን አስደንጋጭ አደጋ ተከትሎ የልጆቹ እናት ማቲ ማያ ታማንግ በጭንቀት ልጆቿን መፈለግ ጀመረች፡፡

ከብርቱ ፍለጋ በኋላ እናት ማቲ ማያ ታማንግ አንደኛውን ልጇን በሕይወት ስታገኝ÷ የ8 ዓመቱን ዞያል ጋሊ ግን ማግኘት አልቻለችም ነበር፡፡

ሆኖም ዞያል ጋሊ አደጋው እንደተከሰተ በፍጥነት ወደ ጫካ በመሮጥ ለሰዓታት ዛፍ ላይ በመውጣት ራሱን ከጎርፍ አደጋ የታደገ ሲሆን ÷ በኋላም የነፍስ አድን ሠራተኞች ከተፈጥሮ ቁጣ ጋር ሲታገል አግኝተውት ወደ ሆስፒታል ወስደውታል፡፡

የ8 ዓመቱን ዞያል ጋሊ አድራሻ ለማግኘት በተደረገው ብርቱ ጥረት የሬውተርስ ጋዜጠኛ ሳህና ባይራቻሪያ የእናቱን ስልክ ማግኘት በመቻሏ እናትየው ታዳጊው ወደሚገኝበት ሆስፒታል እንድትመጣ በማድረግ እናት እና ልጇን ማገናኘት ችላለች፡፡

እናት ማቲ ማያ ታማንግ “ልጄ በጎርፍ አደጋው ለሕልፈት ተዳርገዋል ተብለው በፖሊስ ከተገለጹት 580 ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ አልነበረም፤ ነገር ግን በሕይወት ይገኛል ብዬም አላሰብኩም ነበር” ስትል ለሬውተርስ ተናግራለች፡፡

ከአደጋው ለመትረፍ ባደረገው ጥረት ታዳጊው የአንድ እግር ስብራት እንዲሁም ፊቱ ላይ የመቁሰል አደጋ የደረሰበት ሲሆን÷ አሁን ላይም በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ዘገባው አመልክቷል፡፡

በሚኪያስ አየለ