አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ታይላንድ በጂኦግራፊ የተራራቁ ሀገራት ናቸው። አንድ ግዙፍ ታሪክ ግን ያቀራርባቸዋል፤ የዓለም ታሪክ ሀገራቱን “በቅኝ ግዛት ያልተንበረከኩ” ብሎ መዝግቧቸዋል።
ሁለቱም ሀገራት በ19ኛው እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን የነበረውን የአውሮፓ ቅኝ ግዛት ማዕበል ተቋቁመው ሉዓላዊነታቸውን ጠብቀው ማቆየት የቻሉ ታሪክ ተጋሪዎች ናቸው።
በቀድሞ ስሟ ሲያም (የአሁኗ ታይላንድ) በ19ኛው ክፍለ ዘመን እንግሊዝና ፈረንሳይ በደቡብ ምስራቅ እስያ ሰፊ ግዛቶችን ሲቆጣጠሩ፣ በሁለቱ ኃያላን መንግሥታት መካከል ስትራቴጂያዊ ሚዛንነቷን ተጠቅማ ነፃነቷን ጠብቃለች፤ የታይላንድ ጥበበኛ መሪዎች ሀገራቸውን በዲፕሎማሲና በፖሊሲ ማሻሻያዎች ከቅኝ ግዛት ታድገዋል።
በተመሳሳይ ወቅት አውሮፓ አፍሪካን ስትቀራመት ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ጣሊያንን በማሸነፍ ነፃነቷን ያስጠበቀች ሀገር ሆና ተመዝግባለች።
ለሁለቱም ሀገራት ታሪካቸው የብሔራዊ ኩራት ምንጫቸው ነው። ይህ የታሪክ ተጋሪነት በሁለቱ ሀገራት መካከል የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እርሾ ሆኗል። ይህ የጋራ ትርክት በሁለቱ ሀገራት መካከል የመከባበርና የመተማመን መንፈስ እንዲፈጠር አስተዋፅኦም አድርጓል።
ታይላንድና ኢትዮጵያ መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በ1956 ዓ.ም የጀመሩ ሲሆን ÷ ይህንን ግንኙነታቸውን ተከትሎም የንግድና የባሕል ግንኙነታቸውን አጠናክረው ቆይተዋል፡፡ ከትናንት እስከ ዛሬ የተሻገረው የሀገራቱ ግንኙነት ኢትዮጵያ ለምትከተለው ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ እንደማሳያ የሚቆጠር ነው።
ሁለቱ ሀገራት የዜጎችን ጥበቃን በተመለከተ ስምምነቶች ያሏቸው ሲሆን ታይላንድ ወደ ማይናማር ተጭበርብረው ተወስደው የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ደህንነታቸውን ተጠብቆ እንዲመለሱ ድጋፍ አድርጋለች።
ኢትዮጵያና ታይላንድ የጋራ የኢኮኖሚ እድገት መሻትን ይጋራሉ፤ ይህም ለአዳጊ ባለኢኮኖሚ ሀገራቱ በደቡብ ደቡብ ቅኝት ሌላ የትብብር መድረካቸው ነው። እንዲሁም ባንኮክ በህክምና ቱሪዝም ሰፊ ልምድ ያላት ሲሆን አዲስ አበባ በዘርፉ የአፍሪካ ፊት ቀደም የመሆን ግብ አስቀምጣለች።
በብራዚል በተካሄደው የብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ ወቅት የታይላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪስ ሳንጋምፖንሳ ከኢትዮጵያ አቻቸው ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ጋር በመገናኘት በተለይ በቱሪዝምና በህክምና አገልግሎት ዘርፎች የትብብር እድሎችን መርምረው ነበር።
ዛሬ ይህ እያደገ የመጣ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። የታይላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሃሳክ ፉዋንግኬትክየው በኢትዮጵያ እያደረጉት ያለው የስራ ጉብኝት የመጀመሪያው በከፍተኛ ሃላፊነት ያለ የታይላንድ መሪ ይፋዊ ጉብኝት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ይህም ታይላንድ ከአፍሪካ አጋሮቿ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሳደግ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። ዛሬ ሁለቱ ሀገራት የተለያዩ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ጠቃሚ የማምረቻና የሎጂስቲክስ ማዕከል ተደርጋ የምትታይ በመሆኗ፣ ይህ ጉብኝት በኢትዮጵያና በታይላንድ መካከል እያደገ የመጣውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ተደርጎ ተወስዷል።
በአፈወርቅ እያዩ