የሀገር ውስጥ ዜና

የጋዜጠኛዋ ጦርነት ናፋቂነት እና የካይሮ አሮጌ ትርክት

By emebet sisay

August 29, 2026

ዓለም በበርካታ የጂኦ ፖለቲካ ቀውሶች እየታመሰች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ ባለፈው ሳምንት በስመ ጋዜጠኝነት የታየው አሳዛኝ ተግባር አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል፡፡

አሜሪካዊት ጋዜጠኛ ሃድሊ ጋምብል የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ ጋር ያደረገችው ቆይታ፣ ከመደበኛ የፖለቲካ ትንታኔ ይልቅ ወደ “ሆሊውድ የጦርነት ፊልም ዳይሬክተርነት” ያጋደለ አስገራሚ ክስተት ሆኖ አልፏል።

ጋዜጠኛዋ የሰላም እና የመፍትሔ ድልድይ መሆን ሲገባት፣ ሁኔታዎችን ወደ ሀገራት ግጭት እንዲያመሩ የሚያደርግ አካሄድ መከተሏ አሳዛኝ ትዕይንት ሆኗል።

የግብፅን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊት ለፊት አስቀምጣ፣ “በአፍሪካ ትልቁ ወታደራዊ ኃይል ኖሯችሁ ካልተጠቀማችሁበት ጥቅሙ ምንድነው?” ብላ መጠየቋ፣ ሚዲያው ካለበት ገለልተኛና ገንቢ ሚና ያፈነገጠ ነው።

ይህ አቀራረብ በሌላ አነጋገር “ለምን ወታደራዊ ርምጃ አትወስዱም?” የሚል አደገኛ አንድምታ ያለው ሲሆን÷ የጋዜጠኝነትን መድረክ ወደ ጦርነት አውድማነት ለመቀየር የተደረገ ሙከራ ይመስላል።

የቴሌቪዥን ፕሮግራምን እንደ ተከታታይ የጦርነት ፊልም አድርጎ ማቅረብ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ውስጥ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው አካሄድ ነው።

ለዚህ ዓይነቱ የጋዜጠኛዋ ገፋፊነት ምላሽ የሰጡት የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ቢሆኑ፣ ለዘመናት የኖረውንና የተለመደውን የካይሮን ዲፕሎማሲያዊ ስክሪፕት ከመደገም አልቦዘኑም።

“ውሃው ለእኛ የሕልውና ጉዳይ ነው!” የሚለውን ትርክት በድጋሚ በማንሳት፣ ግብፅ በዙሪያዋ ያሉትን ቀጣናዊ ቀውሶች (እንደ ጋዛ፣ ሊቢያ እና ሱዳን ያሉትን) ችላ ብላ ትኩረቷን በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ላይ ለማድረጓ በምስካሬነት የሚቀርብ ነው፡፡

ሚኒስትሩ የጋዜጠኛዋን ገፋፊነት ለማለዘብ “የኢትዮጵያን ህዝብ እንወዳለን” የሚል ዲፕሎማሲያዊ ምላሽ ለመስጠት ቢሞክሩም፣ ግብፅ በተግባር አሁንም ዜሮ-ድምር አመለካከትን የሙጥኝ ማለቷ፣ በንግግር እና በውጤት ላይ የተመሰረተ መፍትሄን ለማምጣት ያላትን ዝግጁነት ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል።

እውነታው ግን የመድረክ ላይ ጩኸቶች መሬት ላይ ያለውን ሀቅ ሊቀይሩት አለመቻላቸው ነው።

ይህ ታሪካዊ ፕሮጀክት የኢትዮጵያን ብርሃን የማግኘት መብት ያረጋገጠ እንጂ በማንም ላይ ጉዳት ለማድረስ የታለመ አለመሆኑ በተግባር ታይቷል።

አሁን ላይ ወደ ኋላ ተመልሶ ስለ ግድቡ ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ዛቻዎችን ማሰማት፣ ወይም ዲፕሎማሲያዊ ክሶችን መደርደር ጊዜው ያለፈበትና ፋይዳ ቢስ አካሄድ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል።

ይህን ተጨባጭ እውነታ መሠረት ያደረገው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ እና የልማት ፖሊሲ “ከመጮህ ይልቅ በተግባር ማሳየት” በሚል ጽኑ መርህ የሚመራ ሆኗል። ሀገሪቱ ውጫዊ ጫናዎችን በትዕግስት እያለፈች፣ ሙሉ ትኩረቷን በልማት ላይ አድርጋለች።

ከጉባው ታላቅ የኃይል ማመንጫ ተነስቶ እስከ ምስራቋ ጎዴ የተዘረጋው የልማት ጉዞ፣ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና መንገድ በግልጽ ያሳያል። በአንድ በኩል ኤሌክትሪክ እያመነጨች፣ በሌላ በኩል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የስንዴ ምርትን እያሳደገች፣ እንዲሁም ከተሞቿን በዘመናዊ ኮሪደሮች እያለማች ትገኛለች።

ይህ አይነቱ ስራ ላይ ብቻ ያተኮረ አካሄድ፣ ውጫዊ ትንኮሳዎችን በውጤት የማምከን የላቀ ስትራቴጂ ነው።

ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እና እንደ ሃድሊ ጋምብል ያሉ ጋዜጠኞች ስለ አፍሪካ ጉዳዮች ሲዘግቡ፤ ስለ አህጉሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ፣ ስለ ሉዓላዊነትና የጋራ ተጠቃሚነት መርሆች ጥልቅ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል።

ወታደራዊ ኃይል ሰላምን ለማስጠበቅ እንጂ ጎረቤትን ለማስፈራሪያ የሚውል አለመሆኑን መገንዘብ የዘመናዊ ዲፕሎማሲ መሠረት ነው። ካይሮም አሮጌውን ትርክቷን ትታ፣ አዲሱን የትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት እውነታ ብትቀበል ለቀጣናው ሰላም ይበጃል።

በኃይለኢየሱስ መኮንን