አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የአንድን ሀገር ማህበራዊ ትስስር የሚያጠናክርና የዜጎችን የመረዳዳት እሴት የሚያጎለብት የቅንነት መንገድ ነው።
እያንዳንዱ ሰው ያለው ትንሽ እውቀት፣ ጊዜ ወይም ጉልበት የሌላውን ሰው ህይወት ሙሉ በሙሉ የመቀየር አቅም አለው።
የበጎ ፍቃድ እንያንዳንዱ ሰው ያለ ትርፍ ፍለጋ፣ ያለ ክፍያ፣ በቀና ሀሳብ ለሚያውቋቸውም ለማያውቋቸውም ሰዎች፤ ለማህበረሰብና በጠቅላላው ለሕዝብ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ነው፡፡
ሰው ተኮር እሳቤ መለያው የሆነው የመደመር መንግሥት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና ሌሎችም የህብረተሰባችን መልካም እሴቶች እንዲጎለብቱ አስቻይ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።
በጎ ፍቃደኝነት በቋንቋ፣ በሀይማኖትና በብሔር ወይም በሌላ በማንኛውም የልዩነት መስፈርት የሚገደብ ሳይሆን በራስ ተነሳሽነት የሚከናወንና የህሊና እርካታ የሚያስገኝ ተግባር ነው።
በጎነት ለራስ ስንቅ ነው፤ በክረምትም ሆነ በበጋ አቅመ ደካሞችንና ህጻናትን መደገፍ፣ በሀገር ልማት ላይ የራስን አስተዋጽኦ ማበርከት ከአንድ ወጣት የሚጠበቅ ተግባር በመሆኑ ወጣቶች በተለያዩ የበጎ ፍቃድ ስራዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
በዋናነትም በደም ልገሳ፣ የመማሪያ ቁሳቁስ በማሟላት፣ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርትን በመስጠት፣ የትምህርት መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት እንዲሁም በሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት፣ አረጋውያንና ወላጅ ያጡ ህፃናትን በመርዳት የበጎ ፍቃድ ተግባራትን በመከወን ላይ ይገኛሉ፡፡
በተጨማሪም አካባቢን አረንጓዴ በማልበስና በቆሻሻ አወጋገድና ፅዳት አገልግሎት የሀገርን ሀብት ከወጪ በማዳን ኢትዮጵያውያን የሚታወቁበትን እርስ በርስ የመደጋጋፍ ባህል እንዲዳብር አዎንታዊ ሚና ተጫውተዋል።
ይህ ተግባር መተሳሰብና መረዳዳትን የሚያጎለብትና የህሊና እርካታ የሚገኝበት መሆኑን ጠንቅቀው የተረዱ ወጣቶች በቋሚነት ተሳታፊ መሆን ችለዋል፡፡
ይህ በገንዘብ የማይተመን አገልግሎት በብዙ ሀገራት የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ዋና ምሰሶ በመሆን ያገለግላል፤ በዚህ ረገድ የሀገራችንን የእድገት ጉዞ ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት በመሰል ተግባራት በመሳተፍ ለትውልድ የሚሻገር አሻራ ማኖር ይገባል፡፡
በትዕግስት ግዛቸው