የሀገር ውስጥ ዜና

በመደመር እሳቤ ለሀገራዊ አንድነት አዲስ ምዕራፍ የከፈተው ምክክር

By amele Demisew

August 30, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለዘመናት የተሸከመቻቸውን የተወሳሰቡ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ ክፍፍሎች በዘላቂነት ለመፍታት፤ እንዲሁም ጠንካራና አሳታፊ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት የመደመር ፍልስፍና አሻጋሪ ሀሳብ ሆኖ ብቅ ብሏል። የመደመር ፍልስፍና በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ከመግባባት ዴሞክራሲ እና ከምክክር ዴሞክራሲ መርሆዎች ጋር በእጅጉ ይሰናሰናል፡፡ ይህም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል ከግጭትና ከጽንፈኝነት ወደ የጋራ መግባባት፣ ትብብርና ሰላማዊ ውይይት የመቀየር አቅም ያለው የፍልስፍና ማዕቀፍ ነው። በተለምዶ የሚታወቀው የብዙሃን አብላጫ ድምጽ ዴሞክራሲ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዝሃነት ባላቸው ሀገራት ውስጥ አሸናፊና ተሸናፊ የሚፈጥር በመሆኑ፤ ለፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና ለግጭቶች መንስኤ ሆኖ ቆይቷል። በአንጻሩ በመደመር እሳቤ የታቀፈው የመግባባት ዲሞክራሲ ሞዴል፣ የፖለቲካ ስልጣንና ውሳኔዎችን አካታች በሆነ መንገድ በጋራ የመጋራት ባህልን ያቀነቅናል፡፡ በተጨማሪም የሁሉም ብሔሮችና፣ ቡድኖች ድምጽ እንዲሰማ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ፤ የፖለቲካ ልሂቃን እና የህብረተሰብ ክፍሎች በጋራ እንዲሰሩ መንገድ ይከፍታል። ይህ አካታች እሳቤ በኢትዮጵያ ለተካሄደው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ጽኑ የፖለቲካ እና የፍልስፍና መሰረት ጥሏል፡፡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከምሁራን እና ከሲቪል ማህበራት የተወጣጡ አካላትን በማሳተፍ ያካሄደው የምክክር ሂደት የዚሁ የመግባባት እና የውይይት ዴሞክራሲ ተግባራዊ ማሳያ ነው፡፡ ይህም ዜጎች በሀገራዊ መሰረታዊ ጉዳዮች እና የታሪክ ጠባሳዎች ላይ በነጻነት በመወያየት ልዩነቶቻቸውን በሰለጠነ መንገድ እንዲያቀራርቡ አስችሏቸዋል። ከዚህም ባሻገር በምክክር ዴሞክራሲ መርህ መሰረት ውሳኔዎች የሚወሰኑት በኃይል አፈሙዝ ወይም በአብላጫ ድምጽ ጫና ሳይሆን በምክንያታዊ ውይይት እና በጋራ መግባባት ላይ በመሆኑ፤ የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ሀገር አሸናፊ የምትሆንበት አቅጣጫ እንዲይዝ አግዟል። ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያሉ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በሂደቱ መሳተፋቸው ያልተወከለ አመለካከት እንዳይኖር እና ለሁሉም የሚሆን የጋራ ሀገራዊ ራእይ እንዲቀረጽ መንገድ ከፍቷል። በአጠቃላይ በመደመር እሳቤ የታገዘው የመግባባትና የውይይት ዴሞክራሲ ባህል ኢትዮጵያን ከኋላቀር የኃይል ፖለቲካ ባህል በማላቀቅ፤ ለዘላቂ ሰላም፣ ለዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ እና ለአካታች ሀገራዊ ዕድገት የሚሆን ጽኑ መሰረት ጥሏል፡፡ ሀገራዊ ምክክሩም የዚሁ እሳቤ ውጤት ማሳያ በመሆን ለሀገራዊ አንድነት አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። በአብረሃም አበራ