የሀገር ውስጥ ዜና

ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያንና ህዝቦቿን አሸናፊነት ያሳየ ታሪካዊ ክስተት ነው

By betelhem girma

August 30, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገረ መንግሥት ግንባታ የጋራ ጥረትና መግባባት የሚፈልግ ከመሆኑ ባሻገር የበርካታ ሂደቶች ውጤት ነው፡፡

ከእነዚህም ወሳኙን ሚና የሚጫወተው ምክክር ነው፤ ምክክር ቁርሾዎችን መፍታት፣ የታሪክ ስብራቶችን መጠገን መነሻው ሲሆን በብዙ ያለመግባባት ሂደቶች ውስጥ አልፎ ተደማምጦ ወደ መግባባት በመሻገር መድረሻውም የጋራ ሀገረ መንግሥት መገንባት ነው፡፡

ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም እንደሚሉት ጠንካራ ሀገረ መንግሥት መገንባት በአንድ ጀምበር ወደ ውጤት የሚደርስ ሳይሆን፤ የሁሉንም ዜጋ ትዕግስት፣ መቻቻልና የመስራት ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡

የተከሉት ሁሉ በአንድ ቀን ፍሬው አይበቅልም፣ አይበላምም በመሆኑም ለትውልድ መሰረት ያላት መልካም ሀገር ማቆየት የምንችለው በተገቢው ሁኔታ የተከልናትንና በእንክብካቤ ያቆየናትን ሀገር ነው፡፡

የታሪክ ጠባሳዎች፣ የፖለቲካ ሀሳብ ልዩነቶች የፈጠሩትን አለመግባባት ተረድተው በህዝቦች ዘንድ መከፋፈልን ሊፈጥሩ የሚሹ፣ ኢትዮጵያን የጦርነት ቀጣና ሊያደርጓት የሚሰሩ የተለያዩ አካላት ከጥንት እስከዛሬ ያለማቋረጥ እንቅልፍ አጥተው ይሰራሉ፡፡

የውጪ ባዳዎች በኢትዮጵያ መከፋፈልና የህዝቦች በጋራ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር አለመስራት ውስጥ የእነርሱን ጥቅም ከማስላት የመጣ ነው፡፡ በዚህም የውስጥ አኩራፊ ባንዳዎች በተባባሪነትና ለጥቅም ተገዢነት አብረው ይሰራሉ፡፡

ኢትዮጵያ ግን የሚበጃትን ተረድታ ከታሪክም ትምህርት ወስዳ የቀደመ ክብሯን በሚመጥን መልኩ ምክክርን የመፍትሄ አቅጣጫ አድርጋ ከቀረቡት አጀንዳዎች ላይ በአብዛኛዎቹ በመግባባት ከስምምነት ላይ ደርሳለች፡፡

ምክክሩ ለዘመናት በጦርነት፣ በኃይልና በፖለቲካ ሽኩቻ ሲንከባለሉ የቆዩ የትርክት ስብራቶችም ከጠብመንጃ ይልቅ በሰላማዊ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ስለመቻሉም ትልቅ ማሳያ ነው።

ይህ የምክክር ሂደት መነሻ እንጂ መጨረሻ ባለመሆኑ የቀሩትን አለመግባባቶችም ከጠብመንጃና የጦርነት አዙሪት በመውጣት በዚሁ የውይይት መንገድ መፍታት እንደሚቻል የገለጠ የኢትዮጵያንና ህዝቦቿን አሸናፊነት ያሳየ ታሪካዊ ክስተት ነው፡፡

በቤተልሔም ግርማ