የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያሳዩት የጉባ ብስራት ፕሮጀክቶች

By betelhem girma

August 30, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከቀደመው ጊዜ ጀምሮ በሰዎች መገንባታቸው ጥርጣሬ ውስጥ እስኪገባ የሚያስደምሙ፤ ትናንት የገነባቻቸው ዛሬ ላይ ዓለም እንደ ቅርስና መማሪያነት አድርጎ የሚጎበኛቸው የኪነ ህንፃ ጥበቦች ያላት ምድረ ቀደምት የስልጣኔ ባለቤትነት ሀገር ናት፡፡

ነገር ግን የቀደመ የኩራት ታሪኳ ህዝቦቿን አዘናግቶ ለረጅም ጊዜያት ወደ ኋላ በሚጎትት አዙሪት ውስጥ ስትዳክር ዓለም ቀድሟት የሄደበት ጊዜ ነበር፡፡ የለውጡ መንግሥት ኢትዮጵያን ወደቀደመ ከፍታዋ ለመመለስ የሚያስችሉ ተግባራትን በመፈጸም ላይ ይገኛል፡፡

“አባይ በጣና ላይ እንዴት ቀለደበት፤ ለአንድ ቀን ነው ብሎ ጉባ ከተመበት” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተናገሩለት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ መጠናቀቅን ተከትሎ የጉባ ብስራቶችን ይፋ አድርገዋል፡፡

ይህም የአፍሪካ ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ፣ የኒውክሌር ማበልጸጊያና የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታን ጨምሮ የተለያዩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጉባ ላይ ብስራቶች እንደሆኑ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ህልውና ማስከበርና በዓለም ያላትን ተሰሚነትም ማሳደግ የሚቻለው በጦርነት ዘመቻዎች ላይ በመሳተፍ ብቻ ሳይሆን፤ ለሀገር ልማት የሚሆኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በመገንባትም ጭምር ነው፡፡

መፍጠርና መፍጠን ላይ የሚያጠነጥነው የመደመር መንግሥት ከዓለም ትይዩ ለመጓዝ የሚያስችለውን አዳዲስ ፕሮጀክቶችን የመጀመርና የተጀመሩትንም የመጨረስ አቅሙን በተግባር አሳይቷል፡፡

የእነዚህ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዘላቂነት ያለው እድገትን ከማረጋገጥ ባሻገር የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረጉ የቀጣናውን ተሰሚነት የሚጨምሩ ናቸው፡፡

በጋራ ሀገር ጉዳይ ላይ መተባበርና አብሮ መቆም የኢትዮጵያውያን መገለጫ በመሆኑ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የሌሎችን ድጋፍ ሳይሹ እንደገነቡ ሁሉ ሌሎችንም ግዙፍ ፕሮጀክቶች የመገንባት አቅም እንዳላቸው ያመላከቱበት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ፤ ጀምሮ የመጨረስን አቅም ያሳየ ለሌሎች ፕሮጀክቶች ግንባታ ተነሳሽነትም የፈጠረ ታሪካዊ ክስተት ነበር፡፡

የቢሾፍቱ ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት በአፍሪካ ግዙፉ የአውሮፕላን ማረፊያ በመሆን 60 ሚሊየን ገደማ የሚሆኑ ተሳፋሪዎችን በዓመት ለማስተናገድ የሚችል ለሀገሪቱ ግዙፍ አቅምን የሚገነባ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህም ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃትን ይፈጥራል፡፡

ኢትዮጵያ ከናይጄሪያዊው ባለሀብት አሊኮ ዳንጎቴ ጋር ያደረገችው በዓመት እስከ 3 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የዩሪያ ማዳበሪያን የሚያመርተው የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ የአርሶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል ለግብርናው ዘርፉ ከሚያደርገው አስተዋፅኦ ባሻገር ኢትዮጵያ ከውጪ ለማስገባት የምታወጣውን ምንዛሬ የሚቀንስ ነው፡፡

ለኃይል ማመንጫነት የሚውል የኒውክሌር ሀይል ማመንጫ ግንባታ የሚውል ስምምነትን ከሩሲያ ጋር አድርጋለች፡፡ ይህ የቴክኖሎጂውን ዘርፍ ለማሳደግና የዓለም አቀፍ ተፅእኖ ፈጣሪነትን በማጠናከር ረገድ ሚናው ትልቅ ነው፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ 5 የኢኮኖሚ ምሰሶ አድርጋ ላስቀመጠቻቸው የግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና አይሲቲ ዘርፎችን ለማሳካት በማለም እነዚህን የጉባ ብስራት ፕሮጀክቶች በመተግበር ለዘላቂ እድገት እየሰራች መሆኗን ያመለክታል፡፡

በቤተልሔም ግርማ