አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ምክክሩ ለመጪው ትውልድ የልዩነት መፍትሔው ምክክር መሆኑን ያስገነዘበ ታሪካዊ ጉባዔ ነው አለ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት።
የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አሕመድ ሁሴን እንዳሉት፤ የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ከውጤቱ ባሻገር አስተማሪ የሆነና ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው።
የምክክር ጉባዔው የተለያየ አቋም ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበትና ልዩ ልዩ ሀሳቦች የተንጸባረቁበት እንደሆነ በመግለጽ ለረጅም ዓመታት ወደ አለመግባባትና ግጭት ሲመሩ በቆዩ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት ተመክሮባቸዋል ብለዋል።
በምክክሩ ሂደት ተመካካሪዎች አቋማቸውን፣ ፍላጎቶቻቸውንና ሥጋቶቻቸውን በነፃነት የገለጹበት እና በርካታ የውሳኔ ሀሳቦች የቀረቡበት መሆኑን አንስተው ተመካካሪዎች በአብዛኛው አጀንዳ ላይ ከስምምነት በመድረስ በጥቂት አጀንዳዎች ላይ የአማራጭ ሀሳቦችን ማቅረባቸውን አስረድተዋል።
ተመካካሪዎች ለሀገርና ለትውልድ በማሰብ የቆዩ አቋሞቻቸውን ለውጠው ወደ መግባባት የመጡበት ውጤታማ ጉባዔ እንደሆነ እና ይህ ተግባር ለመጪው ትውልድ ልዩነት ተፈጥሯዊ የሆነና መፍትሔውም ምክክር መሆኑን የሚያስገነዝብ መሆኑን አመልክተዋል።
ከምክክሩ የተገኙ ሀሳቦች በፖሊሲና ሕግ ግብዓትነት የሚካተቱ መሆናቸውን ጠቅሰው ለተግባራዊነታቸው በትኩረት መስራት እንደሚጠይቅ በማንሳትም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤትም የበኩሉን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
ከግጭትና የኃይል አማራጭ ከመምረጥ ይልቅ ተቀራርቦ መምከር የበለጠ ጥረት፣ ትዕግስት እና ብስለት የሚጠይቅ ተግባር እንደሆነ እና የግጭት አስተሳሰብን መቀየር የሚቻለው ብሎም መፍትሔ የሚገኘው በምክክር እንደሆነ መገንዘብ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
በተጨማሪም ሕብረተሰቡን ከድህነት ለማላቀቅ፣ በሰላም ተንቀሳቅሶ መስራት፣ መነገድና ምርቱን በገበያ መሸጥ እንዲችል ምክክርና ድርድርን መምረጥ እንደሚገባ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።