አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት በሁሉም ዘርፎች በተቀናጀ መልኩ እያከናወናቸው ባሉት ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ።
ከነዚህም መካከል አንዱና ዋነኛው የግብርና ዘርፍ ሲሆን፣ ይህ ዕይታ በዘርፉ እመርታዊ ለውጥ እንዲመዘገብ አስችሏል።
በሐረሪ ክልልም በመደመር መንግሥት ዕይታ በተከናወኑ የተቀናጀ የግብርና ሥራዎች ምርትና ምርታማነት አበረታች ደረጃ ላይ ደርሷል።
በገበያ ተኮር ምርቶች ዓይነት፣ ብዛትና ጥራት ላይ የታየው ለውጥ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ከማረጋገጡም በላይ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት እንዲሸጋገር አድርጎታል።
በክልሉ ከተማ እና ገጠር ወረዳዎች ባለፉት ዓመታት በሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በእንስሳት ሀብት ልማት፣ በሌማት ትሩፋት እንዲሁም በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በተለይም በገጠር ወረዳዎች የተከናወኑ የመስኖ ልማት ሥራዎች የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያ አቅርቦት ከፍተኛ እገዛ እያደረጉ ይገኛሉ።
በሌላ በኩል የዝናብ እጥረትና በሽታን በመቋቋም በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱ የማሽላና የበቆሎ ሰብሎችን ምርታማነት ማሳደግ መቻሉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል።
በቀጣይም የተቀናጀ የግብርና ሥራው ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን፣ አርሶ አደሩን በሁሉም ዘርፎች የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዕቅዶች ተግባራዊ ይደረጋሉ።