አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የፖለቲካና ማኅበራዊ ታሪክ ውስጥ በኃይልና በነፍጥ ሽኩቻ የተበላሹ ታሪካዊ ስብራቶችን በሠለጠነ የምክክር ባህል ለመጠገን የተወጠነው ሀገራዊ ሂደት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፋች ሁነቶች የተስተናገዱበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
ከአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን፣ ዳያስፖራዎች እና የቀድሞ ታጣቂዎችን ጨምሮ ከ4 ሺህ በላይ ተመካካሪዎች የተሳተፉበት ጉባኤ የብሔራዊ መደማመጥ መድረክ ከመሆኑ በላይ የሀገር ግንባታን መሠረታዊ ባህርይ አመላክቷል።
ይህ ሰፊ ውይይት የተካሄደባቸው ስምንቱ ዋና ዋና አጀንዳዎች ከሀገር ግንባታ እና የመንግሥት አወቃቀር እስከ ተቋማት ግንባታ፣ ሰላም፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንዲሁም መልካም አስተዳደር በሕዝቦች መካከል ለዘመናት የቆዩ ጥልቅ የሐሳብ ልዩነቶችን ፊት ለፊት ለመጋፈጥ ያስቻሉ ነበሩ።
በምክክሩ ሂደት ላይ የተንጸባረቁት የሐሳብ ፍጭቶችና ውዝግቦች የፖለቲካ ምህዳሩን ከደመኝነትና ከአመጽ አዙሪት አውጥቶ ወደ እርጋታና ስክነት የማሸጋገር አቅም እንዳለው ያሳዩ ናቸው።
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በዚህ ጉባኤ መዝጊያ መርሐ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ሀገራዊ ምክክሩ የቆየውን ነባር ባህል የዘመናዊ ሀገር ግንባታ ካስማ በማድረግ “ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው” የሚሉትን ስጋቶች በትዕግሥት እና በበሰለ ውይይት ለመሻገር የሚያስችል መደላደል ፈጥሯል።
በሂደቱ የተነሱ በርካታ አጀንዳዎች ስምምነት ላይ ሲደርሱ ጥቂት ያልተቋጩ ውዝግቦች ወደፊት እንዲተላለፉ መደረጉ የውይይቱን ጥልቀት እና የሀገራዊ ጥያቄዎችን ውስብስብነት ያሳያል።
የሂደቱ ትልቁ ስኬት በሁሉም ጉዳዮች ላይ ፍጹም ስምምነት ላይ መደረጉ ሳይሆን በልዩነቶች ውስጥም ቢሆን እርስ በእርስ መደማመጥና መከባበር መቻሉ እንደሆነ የምክክሩ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረ ሥላሴ ይናገራሉ።
ይህም ከተገለሉ ማህበረሰቦች እስከ ፖለቲካ ተዋንያን ድረስ የነበረውን ስብራት በማስቀረት ማህበራዊ እምነትን፣ ፖለቲካዊ አሳታፊነትን እና ሀገራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ መሠረት የጣለ መሆኑንም አመልክተዋል።
ሆኖም ሀገር ግንባታ በአንድ ጉባኤ፣ በውሳኔዎች ስብስብ ወይም በአንድ የፖለቲካ ትውልድ የምሽት ጥረት ተጠናቆ የሚያበቃ የታሪክ ክስተት አይደለም። የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ሲናገሩ «ምክክር ይጀመራል እንጂ በማግስቱ አያልቅም» ይላሉ።
በጉባኤው የተለቀሙት ምክረ ሐሳቦችና አጀንዳዎች ወደየክልሎቹ በመመለስ ለሁለንተናዊ የውስጥ ውይይት መነሻ የሚሆኑ እንጂ የመጨረሻው ምዕራፍ እንዳልሆኑም ነው የጠቆሙት።
የሀገረ መንግስት ግንባታ በአንድ በጉባኤ በተገኙ ስኬቶች ብቻ የሚጠናቀቅ ሳይሆን በሂደቱ ቀጣይነት፣ በተቋማዊ መተካካት እና በትውልድ ቅብብሎሽ ላይ ሲመሰረት በመሆኑ በፖለቲካ አውዱ ውስጥ የመደማመጥ፣ የመከባበር እና የመተማመን ባህል መስፋፋቱ ትልቅ ስኬት ሆኖ ይታያል።
በመሳሪያ ኃይል የሚመጣ አሸናፊነት ዘላቂ ሰላምንና መፍትሔን እንደማያስገኝ ተረድቶ፣ ልዩነቶችን የመበልጸጊያ እንጂ የመለያያ አጀንዳ አለማድረግ የነገዋ ኢትዮጵያ መሠረት ነው።
ይህ ሂደት በተከፈተው የምክክር በር በኩል ትውልድን አጋምዶ የሚያሻግር፣ ከተቃርኖ የጸዳ የጋራ ራዕይን የሚቀርጽ እና የሀገረ መንግስት ግንባታን እንደ ቀጣይ ጥበብ የሚቀበል ዘላቂ የትውልድ አደራ መሆኑን በግልጽ ያሳያል።
በዮናስ ጌትነት