አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በምስራቅ እና በሰሜን አፍሪካ የጂኦፖለቲካ መድረክ ላይ የካይሮ የውጭ ፖሊሲ ለዘመናት አንዱ እና ዋናው መመሪያ “ኢትዮጵያን ማዳከም” ሆኖ ቆይቷል።
የግብፅ የፖለቲካ ሊቃውንት እና ገዢዎች የውስጥ የፖለቲካ ውጥረቶቻቸውን ለማስወገድ፣ የህዝብን ትኩረት ለመቀየር እና የብሔራዊ አንድነት ስሜት ለመፍጠር የዓባይን ወንዝ እንደ ህልውና ጉዳይ በመቅረፅ ኢትዮጵያን የጋራ ስጋት አድርገው የማቅረብ ስትራቴጂ ይከተላሉ።
ይህ አካሄድ በዘመናዊ ዲፕሎማሲ የተፈጠረ ሳይሆን፣ ስር የሰደደ የታሪክ እና የጂኦፖለቲካ ስሌት ውጤት ነው።
የግብፅ መንግሥታት የዓባይን ወንዝ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ወታደራዊ ጥረቶችን ጭምር ስለማድረጋቸው የታሪክ ድርሳናት በጎላ ሁኔታ የሚያስረዱት እውነታ ነው። ታዋቂው የታሪክ ተመራማሪ ሪቻርድ ፓንክኸርስት እና ባህሩ ዘውዴ (ፕ/ር) በጥናቶቻቸው እንደሚያስረዱት÷ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በእስማኤል ፓሻ የሚመራው የግብፅ ግዛት “ታላቋን ግብፅ” ለመስራት እና የዓባይን መነሻ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር አልሞ ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ ከፍቶ እንደነበር ያስረዳሉ።
ከአውሮፓ እና ከአሜሪካ የጦር አዛዦችን እና ዘመናዊ መሳሪያዎችን ጭምር በማሰለፍ በፈረንጆቹ 1874 እና 1876 በጉንደት እና ጉራ ጦርነት ከፍተው እንደነበር እና ሆኖም የኢትዮጵያ ጀግኖች የግብፅን ዘመናዊ ጦር አጠቃላይ ውድመት በማድረስ በታሪክ ትልቅ ሽንፈትን አከናንበው መመለሳቸውን ይጠቁማሉ።
የታሪክ ተመራማሪው ሃጋይ ኤርሊክ “Ras Alula and the Scramble for Africa” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት÷ የጉንደት እና የጉራ ሽንፈት ግብፅ በወታደራዊ ኃይል ኢትዮጵያን ማንበርከክ እንደማትችል ያስመሰከረ እና የፖለቲካ ስትራቴጂዋን ከቀጥታ ጦርነት ወደ “የውስጥ አለመረጋጋት መፍጠር” እና “ዲፕሎማሲያዊ ከበባ” እንድታዞር ያስገደደ ክስተት እንደነበር ያትታል።
ግብጽ በወታደራዊ ኃይል ያልተሳካላትን አላማ ለማሳካት የካይሮ መንግሥታት ቀጥሎ የተከተሉት መንገድ የኢትዮጵያን የውስጥ አንድነት ማላላት ነው። ኢትዮጵያ በሰላም እና በልማት ከተራመደች፣ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ከተገነባ እና በናይል ተፋሰስ ላይ ያላት የተፈጥሮ መብት ወደ ኢኮኖሚያዊ አቅም ከተቀየረ የግብፅ የቀጣናው የበላይነት ያበቃል የሚል ስጋት አላቸው።
ለዚህም ሲባል በኢትዮጵያ ውስጥ የሚነሱ የብሄር፣ የሃይማኖት እና የፖለቲካ ቅሬታዎችን በመጠቀም ለተቃዋሚዎች እና ለውስጥ ባንዳዎች የሎጂስቲክስ፣ የገንዘብ እና የዲፕሎማሲ ድጋፍ ማድረግ።
ኢትዮጵያ በቀጣናው እንዳትረጋጋ ከሱዳን፣ ከሶማሊያ እና ከሌሎች የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ጋር ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ስምምነቶችን በመፍጠር ኢትዮጵያን በጂኦፖለቲካዊ ከበባ ውስጥ የማስገባት ስራ መስራት ላይ ትኩረት አድርገው ይሰራሉ።
የግብፅ መንግሥታት ለዘመናት ለሕዝባቸው ሲያስተላልፉት የኖሩት ትርክት “የዓባይ ውሃ የግብፅ ብቻ ነው” የሚል የብቸኝነት ባለቤትነት አስተሳሰብ ነው። ይህ አስተሳሰብ በቅኝ ግዛት ዘመን በተደረጉ አግላይ ስምምነቶች ማለትም በፈረንጆቹ 1929 እና 1959 ላይ የተመሰረተ እንጂ ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍልን ያካተተ አይደለም።
ነገር ግን ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን በገዛ አቅሟ በመገንባት እና ለአገልግሎት በማብቃት ይህንን የቆየ ሀሰተኛ ትርክት ሰብሮታል። ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እንደረጋገጠችው፣ የህዳሴው ግድብ አላማ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንጂ የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት የውሃ ድርሻ መቀነስ ወይም መጎዳት አይደለም።
ግድቡ ውሃ በያዘባቸው እና በሞላባቸው ዓመታት ሁሉ በግብፅ ላይ ምንም አይነት የውሃ እጥረት አለመከሰቱ የካይሮን የፕሮፓጋንዳ ማሽን አጋልጦታል። በርካታ የግብፅ ምሁራን፣ ገለልተኛ ተንታኞች እና ዜጎች የመንግሥታቸውን የሐሰት ጩኸት በመጠራጠር፣ ግድቡ የታችኞቹን ሀገራት የውሃ ፍሰት እንደማያስተጓጉል እና እውነታው ከካይሮ ፖለቲካዊ ፕሮፓጋንዳ የተለየ መሆኑን መገንዘብ ጀምረዋል።
ኢትዮጵያን በማዳከም ላይ የተመሰረተው የግብፅ የቆየ የፖለቲካ አካሄድ በታሪክም ሆነ በዘመናዊ የጂኦፖለቲካ እውነታዎች መሸነፉ አልቀረም። የዓባይ ወንዝ የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሃብት እንጂ የአንድ ሀገር ብቸኛ ንብረት ሊሆን አይችልም።
የግብፅ መንግሥት ከቀደመው የታሪክ ስህተቱ በመማር፣ ኢትዮጵያን ለማዳከም ከሚሄድበት የሴራ ፖለቲካ ወጥቶ በፍትሃዊነት እና በእኩል ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ ቀጣናዊ ትብብር ማድረግ ብቻ ነው ዘላቂ ሰላምና እድገትን የሚያረጋግጠው።
በታሪኩ ለገሰ