የሀገር ውስጥ ዜና

የክልሉ የማዕድን ሀብት ሕግን መሰረት አድርጎ ይመራል – አቶ አሻድሊ ሐሰን

By sosina alemayehu

August 31, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለው የማዕድን ሀብት ሕጎችንና የተዘረጉ አሠራሮችን መሠረት ባደረገ መልኩ በግልጽነትና በኃላፊነት ይመራል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሐሰን።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከክልል እስከ ወረዳ ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን “የማዕድን ሀብታችን – ለዘላቂ ብልፅግናችን!” በሚል መሪ ሀሳብ በክልሉ የማዕድን ሀብት ልማትና አስተዳደር ዙሪያ ሰፊ ውይይት አካሂደዋል።

አቶ አሻድሊ መድረኩ በዘርፉ የሚስተዋሉ የአሠራር ግድፈቶችና ውስንነቶች በግልጽ የተመዘኑበት እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህም የክልሉ የማዕድን ሃብት ሕጎችንና የተዘረጉ አሠራሮችን ብቻ መሠረት ባደረገ መልኩ በግልጽነትና በኃላፊነት እንዲመራ ጥብቅ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ማዕድኑ ባልተገባ መንገድ ሳይባክን ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለሕዝቡ የኑሮ ማሻሻያ እና ለክልሉ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲውል ማድረግ ላይ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም አስረድተዋል።

ለዚህም የዕድገት ምዕራፍ እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍልና አመራር የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።