የሀገር ውስጥ ዜና

ታይላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ ትብብር ታጠናክራለች

By sosina alemayehu

August 31, 2026

‎አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ‎ታይላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ ትብብር ለማጠናከር ትሰራለች አሉ የታይላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሃሳክ ፉአንግኬትኪኦ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ባደረጉት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወቅት እንዳሉት ፥ ታይላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እና ሁለንተናዊ ትብብሯን ለማሳደግ ትሰራለች።

በዚህም በኢትዮጵያ ያደረጉት የጉብኝታቸው ዋና ዓላማም ይህንኑ ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከርና ታይላንድ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ያላትን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሆነ አብራርተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባ በደቡብ ምስራቅ እስያ እና በአፍሪካ መካከል ዋና የትስስር ድልድይ መሆኗን ገልጸው ሃገራቸው በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን ለመክፈት መወሰኗን ጠቁመዋል፡፡

ታይላንድ በኢንዱስትሪ ልማት እና በግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ረገድ ያላትን መልካም የልማት ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗንም አመልክተዋል።

በተጨማሪም ሀገራቸው ከአፍሪካ ጋር ያላትን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የልማት አጋርነት ለማሳደግ ያለመውን “የታይላንድ-አፍሪካ ተነሳሽነት” የተሰኘ መርሃ-ግብር በልዩ ትኩረት እየተገበረች እንደምትገኝ አስረድተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ የሚደረጉ የጋራ ጉብኝቶችና ተደጋጋሚ ውይይቶች ወሳኝ ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆንም ከዓለም አቀፍ የንግድ ሕጎች እና ኢኮኖሚ ጋር በንቃት እንድትሳተፍ የሚያበረታታ መሆኑንም አብራርተዋል።