ቢዝነስ

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ኩራት የሆነው ቡና

By emebet sisay

August 31, 2026

‎አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለቡና ምርት እና ጥራት በሰጠችው ትኩረት በተያዘው በጀት ዓመት የምንጊዜም ከፍተኛውን የወጪ ንግድ ገቢ ማግኘት ችላለች፡፡

የቡና ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዋና ዋና የግብርና ምርቶች አንዱ ሲሆን ÷ ለብዙ ሀገራት ቀዳሚው የውጭ ምንዛሪ ማግኛ እና የወጪ ምርት ገቢ ምንጭ ነው።

እንደ ኤም ጂ ኮፊ ኤክስፖርት መረጃ በዓለም አቀፍ ገበያ የቡና ንግድ ልውውጥ በየዓመቱ ከ40 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ይገመታል።

ብራዚል በዓለም ቀዳሚዋ የቡና አምራች እና ላኪ ሀገር ስትሆን ÷ የዓለምን የቡና ኤክስፖርት ገበያ 35 በመቶ በመቆጣጠር በየዓመቱ ከ14 ቢሊየን ዶላር በላይ የተጣራ የኤክስፖርት ገቢ ታገኛለች።

ቬትናም፣ ኮሎምቢያ፣ ኢንዶኒዥያ፣ ሆንዱራስ፣ ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ የቡና ምርትን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ተከታዩን ደረጃ የያዙ ሀገራት ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ የቡና ምርቷ በዓለም አቀፍ ገበያ ያለውን ተጽዕኖ እና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እንዲሁም የገበያ ተደራሽነቱን ለማስፋት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፋ ስትሰራ ቆይታለች፡፡

የቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በቅርቡ እንደተናገሩት÷ በዓለም ገበያ የኢትዮጵያን ድርሻ ይበልጥ ለማሳደግ በተለይ በምርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ትልቋ የቡና አምራችና ላኪ ሀገር ስትሆን÷ በአሁኑ ወቅት የቡና ምርት ጥራትና የገበያ ተጽዕኖዋ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ይገኛል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ÷ በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን ምርታማነት ለማሳደግ፣ አቅማቸውን መገንባትና የቡና ጥራትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍና በአፍሪካ ደረጃ ያላትን የገበያ መዳረሻ ለማስፋፋት ስትራቴጅዎች ተነድፈው ተተግብረዋል፡፡ በዚህም ቡናችን በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ከፍተኛ መለኪያ የተቀመጠለት ሆኗል።

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካሉ ጥራት ያላቸው የዓረቢካ ቡና አምራቾች ግንባር ቀደም ብትሆንም፣ ቡናን በጥሬው ስለሚላክ ከገበያው ሙሉ ተጠቃሚ አለመሆናቸን ይነገራል፡፡

በተቃራኒው እንደ ጀርመን እና ስዊዘርላንድ ያሉ የአውሮፓ ሀገራት ቡናን ከውጭ አስገብተው እሴት ጨምረው መልሰው በመላክ ከፍተኛ ገቢ እንደሚያገኙ የትሬድ ኢንተርናሽናል መረጃ ያመላክታል፡፡

የቡና እሴት መጨመር ለኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ዕድገት እጅግ ወሳኝና ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ ምሰሶ በመሆኑ የቡናን እሴት ለመጨመር የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡

በሚኪያስ አየለ