አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልልን ወደ ብልጽግና ለማሻገር የሕዝብ እና የባለድርሻ አካላትን አቅም አሟጦ መጠቀም ይገባል አሉ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፡፡
አቶ አደም ፋራህ በዛሬው ዕለት በባሕር ዳር ከተማ ”አርቆ ማየት አልቆ መስራት” በሚል መሪ ሐሳብ በተካሄደው መድረክ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
አቶ አደም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ በመድረኩ የክልሉ የ2018 በጀት ዓመት የፓርቲ እና የመንግሥት ሥራዎች እቅድ አፈፃፀም መገምገሙን አንስተዋል፡፡
በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመቱ በሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ አፈፃፀም መመዝገቡን ጠቁመው ÷ የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ኦሬንቴሽን መሰጠቱን አመልክተዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት የክልሉን ሕዝብ ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ለማድረግ፣ ሰላምን ለማረጋገጥ እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን መሰራት ስለሚገባቸው ጉዳዮች ምክክር መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
በመድረኩ በክልሉ የወደፊት ጉዞ እና ሕዝባዊ አገልግሎት ዙሪያ ጠንካራ እና ፍሬያማ ሐሳቦች ተንጸባርቀዋል ነው ያሉት አቶ አደም።
በአንጻሩ የሕዝብ እና የሀገር አለኝታ የሆኑ ተቋማትን የሚያፈርስ «ተቋም ገዳይ» የፖለቲካ አካሄድ በጥብቅ መወገዙን አጽንኦት ሰጥተዋል።
የክልሉ ሕዝብ ለመንግሥት እና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ያለው ጠንካራ እምነት እና በሁሉም ዘርፎች የተያዙ ውጥኖች እንዲሳኩ ለሚያደርገው ያልተቆጠበ ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና የሚቸረው ነው ብለዋል፡፡
የአሻራ ፖለቲካን በማጎልበት እና የአመራር ጥበብን ተላብሶ ታሪክ ለመስራት ሁሉንም አቅሞች አሟጦ መጠቀም ቀጣይ የጋራ የቤት ሥራ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ክልሉን ወደ ብልፅግና ለማሻገር፣ የሕዝብ እና የባለድርሻ አካላትን አቅም አሟጦ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡