አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለባህር ዳር ጣና ልብሷ፣ አባይ መቀነቷ ነው፡፡ ሰፊና ፅዱ አረንጓዴ አደባባዮቿ በዘንባባ ዛፎች ከተሸለሙት ሰፊ መንገዶቿ ጋር ለከተማነቷ ውብ ነብስ ይዘሩባታል፡፡
ተፈጥሮ ባገማሸረው ውበቷ ላይ የኢትዮጵያ ከተሞችን መልክ የገለጠው የኮሪደር ልማት ተጨምሮ መልኳን ሥሎ ኩሎታል፡፡ ባሕር ዳር ከተማ በኮሪደር ልማቱ ውበቷ እጥፍ ድርብ ጎልቶ የነዋሪዎቿንና የጎብኚዎችን ቀልብ እየሳበችም ትገኛለች።
በልማቱ የደመቁ ዋና ዋና ቦታዎች የጣና ሀይቆች ዳር ለእግረኞችና ለብስክሌት ነጂዎች አመቺ በሆነ መልኩ ተሻሽሏል። የከተማዋ መግቢያና መውጫ በሮች አዳዲስ ሐውልቶችና የውሃ ፏፏቴዎች ተገንብተውባቸዋል።
የከተማዋ ታዋቂ አደባባዮች ታድሰው ቆንጅተዋል፡፡ ሲመሽ ከጣና ከሚነፍሰው ነፋስ ጋር የምትደርበው ብርሃናማ ጌጥ ሌላ ውበት ያጎናጽፋታል።
እኒህ ብርሃናማ ጌጦች፣ የኮሪደር ልማቱ ያቆነጃቸው አውራ ጎዳናዎች ስራ የፈጠሩላቸው፣ ለጎብኝዎች ጌጦችን የሚሸጡ፣ ከተማዋን የሚያስጎበኙ፣ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ መነቃቃት የሆነላቸው የልማቱ ተጠቃሚዎች ሆነዋል፡፡
ይህ ልማት የከተማዋን የታሪክና የባህል ገጽታ ሳይለቅ ዘመናዊ የከተማ ገጽታን ያላበሰ ውበት ነው፡፡
52 ሺህ ተመልካቾችን እንዲይዝ ተደርጎ እየተገነባ የሚገኘው የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከዚህ ቀደም የታዩበት ችግሮችን በማሻሻል ለከተማዋ ተጨማሪ ውበትና ገቢ ሊሆን ዓለም አቀፍ መስፈርትን ባሟላ መልኩ ግንባታው እየተፋጠነ ነው፡፡
ባህርዳር በዙሪያዋ እንደ ጎርጎራ ያሉ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች የተገነቡ መሆናቸው ለቱሪስቶች መሸጋገሪያ የምትሆንበት ዕድልን ፈጥሮላታል፡፡
የኮሪደር ልማቱ ተጋርዶ የነበረውን የጣና ሀይቅና ዳርቻ ውበት የገለጠ ለነዋሪዎችና ጎብኝዎች ልዩ መዳረሻ የሆነ ነው፡፡ ይህ እይታ ሀይቁን ከመንገዱና ከከተማው ጋር ተሳስሯል፡፡
መሰረተ ልማቶችን ያስተሳሰረው የባህር ዳር ኮሪደር ልማት አሁን ባለው አሠራር የመንገድ፣ የውኃ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮም መስመሮች በአንድ ማዕቀፍ ስር አቀናጅቷል፡፡ በአንዱ ተሠርቶ በሌላው የሚፈርስበትን የሀብት ብክነትም አስቀርቷል።
የባህርዳር አዲስ መልክ በአብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ከተሞች እስከ ምሽት ድረስ የመሥራት ልምድ በመዳበሩ አዲስ እና ጠንካራ የሥራ ባሕል እንዲጎለብት አድርጓል፡፡ የተሠሩት ማሻሻያዎች ለግል ባለሀብቶች እና ለአነስተኛ ነጋዴዎች አዳዲስ እና የተለያዩ የንግድ አማራጮችን አስገኝተዋል።
የኮሪደር መንገዶቹ መዘርጋት ምርት እና አገልግሎት በቀላሉ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ በከተማዋ የተሻለ እና ፈጣን የገበያ ትስስር ፈጥሯል። ባህርዳር በኮሪደር ልማት ቆንጅታለች፤ ቁንጅናዋ ለብዙዎች የገቢ ምንጭ ሆኖላቸዋል፡፡
በትዕግስት ግዛቸው