አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ለዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲሁም የሕዝቦችን ትስስር ለማጠናከር የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል አሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፡፡
የ21ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አስተባባሪ ዐቢይ ኮሚቴ በበዓሉ መሪ ዕቅድ ላይ የውይይት መድረክ እያካሄደ ይገኛል፡፡
አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በዓሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልምዳቸውን፣ ተሞክሯቸውን፣ ባህላቸውን እንዲለዋወጡ፣ ዲሞክራሲያዊ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ እድል የሚፈጥር ነው፡፡
ለዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ኢኮኖሚ እድገት እንዲሠሩና በሕዝቦች መካከል አንድነትና ትስስር እንዲኖር በማድረግ በኩል የጎላ አበርክቶ እንደሚኖረውም አመልክተዋል፡፡
በበዓሉ ጉልህ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ከወዲሁ በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት፡፡
መጪው በዓል 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫና ሀገራዊ ምክክር ጨምሮ የሀገራችንን ቀጣይ መንገድ የጠረጉና ወደ አዲስ ተስፋና ምዕራፍ ያሸጋገሩ ሀገራዊ ሁነቶች በተከናወኑበት ማግስት የሚከበር በዓል እንደመሆኑ የተለየ ትርጉም ይኖረዋል ብለዋል፡፡
21ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በኦሮሚያ ክልል የገዳ ስርዓትን ጨምሮ የበርካታ ታሪካዊና ባህላዊ መስህቦች ባለቤት፣ ሕዝቦች ተከባብረው በሚኖሩባትና የብዝሃነት ማሳያ በሆነችው ጅማ ከተማ ይከበራል፡፡
በዓሉ ከልማት፣ ከዲሞክራሲ ግንባታ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ባላቸው ታላላቅ ሀገራዊ ሁነቶች ታጅቦ እንደሚከበር መናገራቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡