የሀገር ውስጥ ዜና

በጋራ ሕልምና አስተሳሰብ የምትገነባ ረቂቅ ተቋም፡ “ሀገር”

By sosina alemayehu

September 01, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር በድንጋይና በኮንክሪት የምትቆም ሳትሆን፣ በሕዝቦቿ የጋራ ሕልምና አስተሳሰብ የምትገነባ ረቂቅ ተቋም ናት። የሀገር ግንባታ የትዕግስት፣ የጋራ ራዕይ እና የዜጎች ዕለት ተዕለት አስተዋጽኦ ድምር ውጤት የሆነ የረጅም ጊዜ ጉዞ ነው።

ሀገራት ከውድቀትና ከድህነት ወጥተው ወደ ተከበሩና የበለጸጉ ሀገራትነት የተሸጋገሩት ልዩነትን በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገርን በማስቀደማቸውና ተቋማዊ መሰረቶችን በመጣላቸው ነው።

በፖለቲካ ሳይንስ ሊቃውንት ዘንድ ሀገራት የሚበለጽጉበትና የሚወድቁበት ዋና ምክንያት የተቋማት ጥራት ነው። በዳሮን አሴሞግሉ እና በጄምስ ሮቢንሰን የተጻፈው “Why Nations Fail” የጋራ መጽሐፋቸው እንደሚያስረዱን÷ የሀገራት እድገት ምስጢር የተፈጥሮ ሀብት ብዛት ሳይሆን አሳታፊ እና ነፃ የሆኑ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት መኖራቸው ነው።

ከግለሰቦች ፍላጎት ነፃ የሆኑ፣ ሕግና ሥርዓትን የሚያስከብሩ ገለልተኛ የፍትሕ፣ የህግ አስከባሪ እና የፋይናንስ ተቋማት ሲገነቡ የሀገር መረጋጋት ይረጋገጣል።

በተጨማሪም የሀገር ግንባታ መሰረቱ ያልተግባቡባቸውን ጉዳዮች በውይይት መፈታት መቻሉ ነው። ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት፣ በጋራ እሴቶች ላይ መስማማት እና ማንም ሰው ከሕግ በላይ እንዳይሆን ማድረግ ለጋራ እድገት መንገድ ይጠርጋል።

ከዚህ አንጻር የሲንጋፖርን ተሞክሮ እንመልከት፦

የእስያ አህጉር ተአምር የምትባለው ሲንጋፖር ከተፈጥሮ ሀብት እጥረትና ከከፍተኛ ድህነት ተነስታ ዛሬ ላይ የደረሰችው በጠንካራ አመራርና በተቋማዊ መዋቅር ነው። በተለይም የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ሊ ኳን ዩ ሙስናን በማጥፋት ሹመት በብቃት ብቻ እንዲሆንና ብቃት ላይ የተመሰረተ አመራር እንዲፈጠር ስራ ሰርተዋል።

በትምህርትና በክህሎት ላይ ከፍተኛ በጀት በመመደብ የሰለጠነ የሰው ሀብት መፍጠር ችለዋል። ለዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ምቹ ሁኔታ በመፍጠርና የወደብ መሰረተ ልማትን በማስፋፋት የዓለም ንግድና የፋይናንስ ማዕከል ለመሆን ስልታዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲን በመዘርጋት ሃገራቸው ዛሬ ላይ እንድትደርስ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ፣ ሀገሪቱ ረጅም ታሪክ ያላት ቢሆንም ውስብስብ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎችን ስታልፍ ቆይታለች። አሁን ላይ እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና ዘላቂ ሀገር ለመገንባት ሰፊ የለውጥ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “መደመር” በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ እንደገለጹት፦”ጠንካራ ሀገር የሚገነባው በጠንካራ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን፣ ነጻ፣ ገለልተኛና በሙያዊ ብቃት የተገነቡ ጠንካራ ተቋማትን በመፍጠር ነው። ተቋማት የሀገር ሕልውና አስከባሪ፣ የግለሰቦችን ፍላጎት አስተካካይና የታሪክ መሸጋገሪያ ድልድዮች ናቸው።”

በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት መንግሥት በዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ ሰርቷል። ከዚህ ውስጥ አንዱ የፍትህ እና የሰብዓዊ መብት ማሻሻያ ነው። የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ በመቅረጽ፣ ፍርድ ቤቶች ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ እንዲሆኑና በህግና በማስረጃ ብቻ እንዲሰሩ ተደርጓል። ያለፉ ቁስሎችን ለመፈወስ የሽግግር ፍትህ ስርዓት መዘርጋቱ የፍትህ አካላትን አመኔታ ጨምሮታል።

ሌላው በኢኮኖሚው ላይ የተደረገው ጥልቅ ማሻሻያ ሲሆን፤ ኢኮኖሚው ከቀደመው የተወሰኑ ዘርፎች ላይ ብቻ ከተንጠለጠለ አሰራር ወጥቶ ወደ ብዝሃ ዘርፍ ማለትም ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና ቴክኖሎጂ እንዲሸጋገር የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ በመደረጉ ውጤት ማምጣት ተችሏል።

የመሰረተ ልማት እና የሰው ሀብት ልማት ላይም የተሰራው ስራ ለጠንካራ ሀገር ግንባታ መሰረት የሚጥል ነው። በትራንስፖርት፣ በኃይል፣ በኮሙኒኬሽን እና በጤና አውታሮች ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች ከሀገር በቀል የትምህርት ፖሊሲ ጋር ተጣጥመው የነገውን ትውልድ ለማንጽ እየሰራ ይገኛል።

ከምንም በላይ ደግሞ ለጠንካራ ሀገር ግንባታ የተግባባ እና አንድነቱ የተጠናከረ ማህበረሰብ መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ፤ ለዚህም መንግስት ታሪካዊ ስብራቶችን ለመጠገንና በዋና ዋና ብሄራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያስችል ዘንድ የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማቋቋም ወደ ስራ በማስገባት ማህበረሰቡ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲፈጥሩ ተደርጓል። ይህም የሰላምና የአንድነት መሰረት እየጣለ ይገኛል።

ብዙ ጸሐፊያን እንደሚያምኑት የሀገር ግንባታ የሒደት ውጤት ነው። በውይይት የሚፈቱ ልዩነቶች፣ ነፃና ገለልተኛ ተቋማት፣ ጥራት ያለው ትምህርት እና የዜጎች የጋራ ጥረት ሲቀናጁ የጸናችና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ይቻላል።

በታሪኩ ለገሰ