አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ)የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሀገራዊ እና ማህበራዊ ኃላፊቱን እየተወጣ ነው አሉ የጉባኤው ዋና ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ 15ኛ የምስረታ በዓል እና 18ኛ ጠቅላላ ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የጉባኤውን ያለፉት ዓመታት ጉዞ በተመለከተ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ጉባኤው በመላ ሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡
ችግሮችን ለመፍታት በጋራ መስራት አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑ በመታመኑ የሃይማኖት አባቶች በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ጉባኤው በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች እንዳይፈጠሩ በማድረግ፣ ጥያቄዎች ካሉ ደግሞ በውይይት መፍታት እንደሚቻል በማሳየት ስራዎች መስራቱን ገልጸዋል፡፡
ማህበረሰቡን የማቀራረብ እና የማስታረቅ ስራዎችን በስፋት እየተሰሩ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
በጋራ በመስራት ውጤት ማምጣት እንደሚቻል በማመን ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት በጋራ በመጓዝ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ግጭት በደረሰባቸው አካባቢዎች ፈጥኖ በመድረስ እና በማረጋጋት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በማጽናናት ጉባኤው የህዝብ አለኝታ መሆኑን አሳይቷል ነው ያሉት፡፡
ጉባኤው ሕዝባዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን አንስተው፤ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በማዘጋጀት የላቀ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡
በቀጣይም ጉባኤው ለሀገር እና ለሕዝብ ጥቅም በትኩረት እንደሚሰራ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በጉባኤው ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴን ጨምሮ የሃይማኖት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች እና አጋር ድርጅቶች ተገኝተዋል፡፡