ኢትዮጵያ በረከተ ብዙ ናት። ተፈጥሮ የሰጣት ሀብት ከሰው ሰራሽ ጥሪቷ ጋር ተዳምረው ብልጽግናዋ አይቀሬ ለመሆኑ ምስክር ናቸው። ቱሪዝም ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ካሉት ምሰሶዎች አንዱ ሆኖ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ውስጥ ልዩ ስፍራ ተሰጥቶታል። ይህ የዕይታ አድማስን ማስፋትና ጸጋዎችን የመመልከት መንገድ ደግሞ ሀብታችን በተገቢው ለመጠቀም እንዲያስችል ታምኖበታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት መጽሐፋቸው “ኢንዱስትሪው በሀገራችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና አካባቢያዊ ሁኔታዎች ውስጥ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዲኖረው እንፈልጋለን።” ሲሉ የመንግሥታቸው መሻት መጠን ምን ድረስ እንደሆነ ያስቀምጣሉ። ባለፉት ዓመታት በከተማም ሆነ በገጠር የሚገኙ መዳረሻዎች ተለይተው፣ ነባሮቹ ተሻሽለው፣ አዳዲሶችም ተገንብተዋል። ይህ ጥረት የመጣውን መልካም ዕድል ወደ ተጨባጭ ጥቅም ለመቀየር የተደረገ ትልቅ እርምጃ ነው። ሆኖም የቱሪዝም እድገት በመሠረተ ልማት ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ዓለም እየተለወጠ ባለበት በዚህ ዘመን፤ ኢትዮጵያን ለዓለም የማስተዋወቅ ኃላፊነት ወደ አዲሱ ትውልድ እጅ እየተሸጋገረ ነው። ወጣቶች በሳይንስና ቴክኖሎጂ በተለይም ማህበራዊ ሚዲያን፣ ክውን ጥበባትንና የአኒሜሽን ጥበብን ተጠቅመው የኢትዮጵያን መልክ ለዓለም እየገለጡ ይገኛሉ። አዲሱ ትውልድ የሀገራችንን ማራኪ ውበቷን፣ የማይደበዝዘውን የታሪክ ትውፊቷንና ድንቅ ብዝሃነቷን ለዓለም በአዲስ መንገድ እያሳየ ይገኛል። ይህ ደግሞ ቱሪዝምን ከባህላዊው የማስተዋወቂያ ስልት አልፎ ዲጂታል ትውልድ ወደሚረዳው ቋንቋ የሚተረጉም አዲስ ድልድይ ፈጥሯል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ ለዚሁ ለአዲሱ ትውልድ አባላት የኢትዮጵያን ድንቅ የብዝሃነት ውበት እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በዓለም ዙሪያ የተበተኑ የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ባህላቸውን፣ ታሪካቸውንና ቅርሳቸውን በአካል የሚያውቁበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። “Connect to your culture”፣ “Connect to your history” እና “Live your legacy” በሚል በተለያዩ ዙሮች የተካሄዱት ጥሪዎች፣ ወጣቶች ከመሠረታቸውና ከፈለቁበት ምድር ጋር እንደገና እንዲተሳሰሩ አድርጓቸዋል። ወጣቶች ጥሪውን ተቀብለው ብቻቸውን አልመጡም። ኢትዮጵያን ዘመናዊ በሆነ የቴክኖሎጂ ቋንቋ ለዓለም ማህበረሰብ የሚያስተዋውቁ አምባሳደሮችም ሆነውላታል። በአዲሱ ዓመት ብዙ ቁጥር ያላቸው የሁለተኛው ትውልድ አባላት ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህ አጋጣሚ ሁለት ገጽታ አለው። አንደኛው፣ እነዚህ ወጣቶች ሀገራቸውን በዓይናቸው አይተው፣ ቅርሶቿን ዳስሰው፣ ከሥረ መሠረታቸው ጋር ጠንካራ ትስስር የሚፈጥሩበት ዕድል ማግኘታቸው ነው። ሁለተኛው፣ ይህ ትውልድ ካለው የቴክኖሎጂ ብቃትና ዓለም አቀፍ ትስስር በመነሳት፣ የተመለከቱትን ውበትና ትውፊት ወደ ዲጂታል ይዘት በመቀየር ለዓለም ማህበረሰብ ማስተላለፍ መቻሉ ነው። ኢትዮጵያ በተፈጥሮ፣ በታሪክና በባህል የበለጸገች ብትሆንም፣ ይህን ሀብት ለዓለም በሚስብ መልኩ የማድረስ ስራ ገና ብዙ ይቀረዋል። የቱሪዝም መሠረተ ልማት መስፋፋትና የሁለተኛው ትውልድ መመለስ ብቻ በቂ አይደሉም፤ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የታገዘ ተረክ ያስፈልጋል። አኒሜሽን፣ ዲጂታል ይዘቶች፣ ማህበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ የሚቀርቡ ውብ ታሪኮች ኢትዮጵያን ከቀድሞው በተለየ ፍጥነትና ስፋት ለዓለም ማስተዋወቅ ይችላሉ። በዚህ መልኩ ቅርስ፣ ትውልድና ቴክኖሎጂ ተዋህደው ኢትዮጵያ ለራሷ ልጆችም ሆነ ለዓለም ማህበረሰብ በአዲስ መንገድ የምትተዋወቅበት ዘመን ተጀምሯል። አዲሱ ዓመት ለዚህ ትስስር መጠናከር ትልቅ አጋጣሚ ይዞ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል። በአፈወርቅ እያዩ