የሀገር ውስጥ ዜና

መጪዎቹ የጳጉሜን ቀናት “የኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ሀሳብ ይከበራሉ

By Hailemaryam Tegegn

September 02, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መጪዎቹ የጳጉሜን ቀናት “የኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ስያሜዎች ይከበራሉ አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ፥ የተገባደደው ዓመት የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ ጅማሮ የሚያመላክቱ ስኬቶች የተመዘገበበት ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ምክንያት መጪዎቹ የጳጉሜን ቀናት “የኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ስያሜዎች እንደሚከበሩ አመልክተዋል፡፡

ጳጉሜን 1 – የእመርታ ቀን – ኢትዮጵያ ከአዝጋሚ እድገት ተላቅቃ ወደ ፈጣንና እመርታዊ የእድገት ምህዋር መግባቷን የምናሳይበት ቀን ነው ብለዋል፡፡

ይህ ዕለት በሁሉም ዘርፍ የተሰሩ ሥራዎችን እመርታዊ ለውጥ የምናስገነዝብበት ይሆናል ነው ያሉት፡፡

ጳጉሜን 2 – የማንሰራራት ቀን – 2018 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከአዝጋሚ እድገት ወደ ሁለንተናዊ ከፍታ መሸጋገር የጀመረችበት ቀን በመሆኑ ዕለቱ የማንሰራራት ቀን የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡

ጳጉሜን 3 – የጽናት ቀን በሚል ስያሜ ይከበራል፤ ኢትዮጵያ ለዘመናት በጽናት ጠብቃው የኖረችውን ነጻነትና ሉዓላዊነት ማስቀጠል የዛሬው ትውልድ ኃላፊነት መሆኑን ለማስገንዘብ ዕለቱ የጽናት ቀን የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል ብለዋል፡፡

ጳጉሜን 4 – የኅብር ቀን

ኢትዮጵያ የብዝሃ ማንነቶች ሀገር እንደመሆኗ ብዝሃነት ጌጣችንና ኅብረታችን ነው፤ ኅብረታችን ደግሞ የአንድነትና የጥንካሬያችን ምንጭ መሆኑን በማውሳት፤ ዕለቱ የኅብር ቀን መባሉን አስረድተዋል፡፡

ጳጉሜን 5 – የነገ ቀን የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ዓላማውም ኢትዮጵያ ነገዋን ዛሬ እየሰራች እንደምትገኝ ማስገንዘብ መሆኑን አመልክተዋል፡፡