የሀገር ውስጥ ዜና

‎የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ዕድል ፈጥሯል – አቶ አሻድሊ ሀሰን

By emebet sisay

September 02, 2026

‎ አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በርካታ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ዕድል ፈጥሯል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ። ‎ ‎በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል “ከመሸመት ወደ ማምረት” በሚል መሪ ሀሳብ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጷጉሜ 1/2018 ዓ.ም የሚቆይ “ኢትዮጵያ ታምርት” ኤክስፖ ተከፍቷል። ‎ ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የመደመር መንግሥት የሀገርን ኢኮኖሚ በጠንካራ መሠረት ላይ ለመትከል እየሠራ ነው። ‌‎ ‎ክልሉ የግብርናውን ዘርፍ ጨምሮ ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆን ሰፊ አቅም እንዳለው ጠቅሰው፥ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ምርትና ምርታማነትን ከጥራት ጋር ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል። ‎ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶችን በማበረታታት ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አንስተው፤ በክልሉ የነባር ኢንዱስትሪዎችን ምርት ከማስተዋወቅ ባለፈ በርካታ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ‎ እድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡

ኤክስፖው የክልሉን ዘርፈ ብዙ አቅሞች ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር መናገራቸውን የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡