አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በመስከረም ወር ለሚከበሩ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላት በቂ የምርት አቅርቦት እንዲኖር ዝግጀት ተደርጓል አለ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ፡፡
የቢሮው ምክትል ሃላፊ እና የገበያ ልማት እና ግብይት ዘርፍ ሃላፊ ደስታ ዶሌቦ ለፋና ዲጂታል እንደገለፁት ፥ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በመስከረም ወር የዘመን መለወጫ እንቁጣጣሽ፣መስቀል እና ያሆዴ በዓላት በድምቀት ይከበራሉ።
በዓላቱን ተከትሎም የፍጆታ ምርቶችን በክልሉ መደበኛ እና የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ፣ የዋጋ ግሽበት እንዳይፈጠር እና የክልሉን የግብይት ስርዓት ለመቆጣጠር በቂ ዝግጀት መደረጉን ተናግረዋል።
በዚህም በመስከረም ወር ለሚከበሩ በበዓላት ከ16 ሺህ 900 ቶን በላይ ጤፍ፣ ከ4 ሺህ ቶን በላይ ስንዴ፣ ከ3 ሺህ 300 ቶን በላይ በቆሎ ለማቅረብ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይ የቁም እንስሳት ግብይትን ለማሳለጥ ከ77 ሺህ በላይ በሬዎች፣ ከ114 ሺህ በላይ በግ እና ፍየሎች፣ ከ160 ሺህ በላይ ዶሮዎች እና ከ2 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ የእንቁላል ምርት ለማቅረብ መታቀዱንም አስገንዘበዋል፡፡
በተጨማሪም 454 ቶን ቅቤ፣ 420 ቶን ማር፣ 395 ሺህ ሊትር በላይ ዘይት እና 7 ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር ምርት በክልሉ በመስከረም ወር ለሚከበሩ በዓላት ይቀርባል ነው ያሉት፡፡
ኃላፊው ምርቶች በበቂ ሁኔታ እና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ፣ ያለ አግባብ የሚደረጉ የዋጋ ጭማሪዎች እንዳይከሰቱ እንዲሁም የሚቀርቡ ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ የሚከታተል ግብረ ሀይልም መቋቋሙን አንስተዋል።
የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምርቶቹን ከሚያቀርቡ ዩኒዮኖች፣አቅራቢዎች እና የህብረት ስራ ማህበራት ጋር ስምምነት መፈፀሙን እንዲሁም ምርቶቹ በነፃነት እንዲዘዋወሩ አስፈላጊው ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ነዳጅን ጨምሮ በፍጆታ ምርቶች ላይ የሚደረጉ አላግባብ የዋጋ ጭማሪዎች ሲታዩ ጥቆማ የመስጠት ባህል እየዳበረ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ እነዚህ ከህብረተሰቡ የሚደርሱ ጥቆማዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ