የሀገር ውስጥ ዜና

መንግሥት የትምህርት ጥራትና ፍትሃዊነትን ለማሻሻል በትኩረት እየሰራ ነው – አቶ አሻድሊ ሀሰን

By sosina alemayehu

September 03, 2026

‌‎አዲስ አበባ – ነሐሴ 28፣ 2018 ዓ.ም (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት የትምህርት ጥራት እና ፍትሃዊነትን ለማሻሻል ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ በትኩረት እየሠራ ነው አሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕስ መስተዳደር አሻድሊ ሀሰን። ‎ ‎የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 28ኛው ክልል አቀፍ የትምህርት ጉባኤ “ጥራትና ፍትሃዊነቱ የተረጋገጠ ትምህርት ለተሻለ የመማር ውጤት” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ይገኛል።

‌‎በጉባዔው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋን(ፕ/ር) ጨምሮ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ተገኝተዋል።

አቶ አሻድሊ ሀሰን በዚሁ ወቅት፣ ‎ባለፉት ዓመታት በተለይም በትምህርት ተደራሽነት ላይ አበረታች ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

‎በተያዘው ዓመት በሀገር አቀፍ እና በክልል አቀፍ ፈተናዎች ላይ የተመዘገበው ውጤት መሻሻል ማሳየቱን አንስተዋል። ‎ ‌‎አክለውም የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እየተደረገ ያለው ጥረት አሁንም ትኩረት ያስፈልገዋል ብለው ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን መወጣት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።‎

‌‎የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር) በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት የተወሰዱ የትምህርት ዘርፉ ርምጃዎች ለውጥ እያስመዘገቡ ይገኛሉ ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመለክታል።

‎ሚኒስትሩ እንደሀገር የተሻሻሉ የቅድመ መደበኛ፣ የአንደኛና የሁለተኛ ፣ እንዲሁም አዳሪ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ መሆኑንና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም 36 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገነቡ አመልክተዋል።

‎ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር) በ2019 የትምህርት ዘመን ለሁሉም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የኮምፒውተር ላብራቶሪ ለማሟላት እየተሠራ መሆኑንና 50 በመቶውን ኮምፒውተሮች ሚኒስቴሩ እንደሚሸፍንም አስረድተዋል።