የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ ከመኪና ሽያጭ ጋር ተያይዞ የሕግ ጥሰት የሚፈጸሙ አካላት ላይ ርምጃ እየተወሰደ ነው

By sosina alemayehu

September 03, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ በመኪና አስመጪዎች እና በኮሚሽን ሠራተኞች በኩል የሚፈጸምን የታክስ ሥወራ እና የግብር ማጭበርበር ድርጊት ለመግታት ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ እየተሠራ ነው አለ የከተማዋ ገቢዎች ቢሮ።

ቢሮው በሰጠው መግለጫ እንደገለጸው÷ በርካታ የመኪና አስመጪዎች ለከተማ አስተዳደሩ የሚገባውን ወርሃዊ ቫት እና ዓመታዊ ግብር ላለመክፈል ሲሉ ሽያጮቻቸውን በኮሚሽን ሠራተኞች አማካይነት እያካሄዱ ይገኛሉ።

በተጨማሪም አብዛኞቹ አስመጪዎች አድራሻቸው ሳይታወቅ ከዋጋ በታች ደረሰኝ በመቁረጥ ከፍተኛ የግብር ስወራ ወንጀል እንደሚፈጽሙ በተካሄደው ጥናት መረጋገጡ ተጠቅሷል።

በታክስ ሕጉ መሠረት በሌሎች ክልሎች የተመዘገቡ አስመጪዎች አዲስ አበባ ውስጥ ሽያጭ ለማካሄድ በሚያስችል መልኩ የክልል ንግድ ፈቃዱን ማስጠቀስ፣ የመሸጫ ቦታ መከራየት እና የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽኖቻቸውን ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል።

ማንኛውም አስመጪ ያስገባውን መኪና መሸጥ ያለበት በኮሚሽን ሠራተኞች አድራሻ ሳይሆን ንግድ ፈቃድ ባወጣበት ቦታ ብቻ ሊሆን እንደሚገባም ቢሮው አሳስቧል።

የኮሚሽን ንግድ ፈቃድ ያላቸው ሠራተኞችም ቢሆኑ በኮሚሽን ፈቃድ የመኪና መሸጫ ግቢዎችን ተከራይተው ከአስመጪዎች የተረከቧቸውን መኪኖች መሸጥ በሕግ ተጠያቂ የሚያደርግ የታክስ ሥወራ ወንጀል መሆኑን ተገንዝበው ከድርጊቱ እንዲቆጠቡ ጥሪ ቀርቧል።

ከመኪና ሽያጭ ጋር ተያይዞ የሕግ ጥሰቶችን የሚፈጸሙ አካላት ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ሕግ የማስከበር ርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ቢሮው ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡