አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የወላይታ ዘመን መለወጫ ጊፋታ በዓል ዋዜማ በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየተከበረ ነው፡፡
የጊፋታ በዓል አከባበር አካል የሆነው የመስህብ ስፍራዎች ጉብኝትም በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄደ ይገኛል::
ጉብኝቱ የጊፋታ መልካም እሴቶችን የማስተዋወቅ ዓላማ ያነገበ ሲሆን፣ የጊቤ 3 ሰው ሠራሽ ሐይቅ፣ ቡሻሻ ጋሯ ፣ የዳሞታ ተራራ እና አጆራ መንትያ ፏፏቴ ከመዳረሻዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የዞኑ ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ፀጋ ፋንታ በዚህ ወቅት÷ እንደሀገር ለቱሪዝም መስክ የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑንና ከኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ እንዲሆን መሠራቱ የጎብኝዎች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን አንስተዋል፡፡
በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ60ሺህ በላይ ቱሪስቶች በዞኑ የሚገኙ የተለያዩ ቱሪስት መዳረሻዎችን መጎብኘታቸውን አስረድተዋል፡፡
ጊፋታ በቅርቡ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች መዝገብ ላይ መመዝገቡ ይታወሳል፡፡
በመለሰ ታደለ