የሀገር ውስጥ ዜና

ብሪክስ ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ሽግግር አዲስ እድል ይዞ መጥቷል – አምባሳደር ነቢዩ ተድላ

By Mikias Ayele

September 04, 2026

አዲስ አበባ፣ነሐሴ 29፣2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ብሪክስ ለአፍሪካ ፋይናንስ፣ ቴክኖሎጂ እና የኢኮኖሚ ሽግግር አዲስ እድል ይዞ መጥቷል አሉ በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢዩ ተድላ፡፡

አምባሳደሩ ከሕንዱ ዲዲ ኢንዲያ የዜና አውታር ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ብሪክስ የአፍሪካ ሀገራት አዳጊ ኢኮኖሚ ካላቸው የስብስቡ አባል ሀገራት ጋር ያላቸውን የንግድ ግንኙነት የሚያጠናክሩበት አዲስ እድል መፍጠሩን አንስተዋል፡፡

የብሪክስ አባል ሀገራት ለአፍሪካ ዋና የንግድ አጋር ናቸው ያሉት አምባሳደሩ፤ በዚህም ብሪክስ ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ሽግግርና እድገት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም በአቅም ግንባታ፣ በቴክኖጂ ሽግግር፣ በግብርና፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በማዕድን እና ቱሪዝም ዘርፎች ለአፍሪካ አዳዲስ እድሎችን ይዞ መጥቷል ነው ያሉት፡፡

አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ፍትሐዊና ትርጉም ያለው ውክልና እንዲኖራት፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት የተደረሰውን የኤዙልዊኒ ስምምነትን ጨምሮ የአፍሪካን የጋራ አቋምና ፍላጎት እንደምትደግፍ አረጋግጠዋል፡፡

ብሪክስ በዓለም አቀፍ ተቋማትና የአስተዳደር ስርዓት ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ኢትዮጵያን ጨምሮ አዳጊ የደቡብ ሀገራት አቋማቸውን እንዲያራምዱ እድል መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡

ተቋሙ የጥንት ስልጣኔና ብዝሃ ባህል ባለቤቷን ሕንድ ጨምሮ የሀያላን ሀገራት ስብስብ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም አባል ሀገራቱ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ  ዘርፎች ልምድ እንዲለዋወጡ በር መክፈቱን አስገንዝበዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ