የሀገር ውስጥ ዜና

በቀጣይ የሚካሄዱ በዓላትና ሀገራዊ ኩነቶች በስኬት እንዲከናወኑ የጋራ ግብረ ኃይሉ የትኩረት አቅጣጫ አስቀመጠ

By Mikias Ayele

September 04, 2026

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ በቀጣይ የሚከናወኑ የጳጉሜ ቀናት መርሐ ግብሮች፣ የአዲስ ዓመት፣ የመስቀል ደመራና የእሬቻ በዓላት እንዲሁም የመንግሥት ምስረታ መርሐ ግብር በስኬት እንዲከናወኑ የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ የዕቅድ ግምገማ በማካሄድ የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ አስቀምጧል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ም/ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ እንዳሉት÷ በቀጣይ በአዲስ አበባ የሚከናወኑ በዓላትና ኩነቶች ከከተማዋ አልፈው ሀገራዊ ትኩረት ያላቸው በመሆናቸው ያለ ምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቁ በጥብቅ ዲሲፕሊንና በተቀናጀ አሠራር መመራት እንዳለበት አመልክተዋል።

ዕቅዱ ውጤታማ እንዲሆን የጸጥታ አካላት በተቀናጀና በተጠናከረ አሠራር ሊያስፈጽሟቸው እንደሚገባ እና ሕብረተሰቡም የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌ/ጀነራል አስራት ደኔሮ በበኩላቸው ÷ ከጸጉረ ልውጥ ግለሰቦች ጋር በተያያዘ የሚኖሩ እንቅስቃሴዎችን ቀድሞ ለመከላከል የተቀናጀ የመረጃ ልውውጥና የትብብር ሥርዓት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ከበዓላትና ከልዩ ኩነቶች የጸጥታ ዝግጅት በተጓዳኝ መደበኛ የወንጀል መከላከል ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን፣ የሀገር መከላከያ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የፌደራልና የኦሮሚያ ፖሊስ እንዲሁም የክፍለ ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ አዛዦችና ሌሎች የጸጥታ አካላት አመራሮች ተሳትፈዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በቀጣይ በመዲናዋ የሚከናወኑ በዓላት እንዲሁም የመንግሥት ምስረታ መርሐ ግብር በስኬት እንዲከናወኑ የጋራ ግብረ ኃይሉ በማንኛውም ሁኔታ በተጠንቀቅ እንደሚቆም መናገራቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።