አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮ-ቴሌኮም ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገውን በጎተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ገለጹ።
ኢትዮ – ቴሌኮም ለ “ስለ እናት” በጎ አድራጎት ድርጅት የ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የገንዘብ እና ለ ውህደት ቅድመ አንደኛና መጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
ዋና ስራ አስፈፃሚዋ እንዳሉት፤ ኩባንያው ከመደበኛ ሥራዎቹ ባሻገር የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።
ኢትዮ ቴሌኮም ከሃምሳ በላይ የበጎ አድራጎት ተቋማት ጋር በትብብር በመስራት ከ22 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ የገለጹት ስራ አስፈጻሚዋ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ የሚደርስ ድጋፍ የሚካሄድበት መሆኑን ተናግረዋል።
የ”ስለ እናት” በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ያሬድ አብዱ በበኩላቸው፤ ኢትዮ ቴሌኮም ላለፉት አምስት ዓመታት በተከታታይ እያደረገላቸው ለሚገኘው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በዘንድሮው የበጎ ፈቃድ ተግባር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የሚውል ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ መሰራጨቱንም ጠቅሰዋል።
የውህደት ቅድመ አንደኛና መደበኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አበበ የኋላወርቅ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮ-ቴሌኮም ለትምህርት ቤቱ ላበረከተው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ሌሎች ተቋማትም የኢትዮ-ቴሌኮምን አርዓያነት በመከተል ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ኢኤአ ዘግቧል።