አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ያለፉት ዓመታት በመንግሥት አዳዲስ እሳቤዎችና በሕዝቡ ትብብር በተለያዩ መስኮች የሚታዩና የሚጨበጡ እመርታዎች ተመዝግበዋል አሉ የተለያዩ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች። የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ም/ሰብሳቢ አቶ በየነ ደሳለኝ÷ የጳጉሜን ቀናት በተለያዩ ስያሜዎች መከበራቸው ሀገሪቱ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች በማንሳት ቀጣይ ስንቅ ለማድረግ የሚያነሳሳ ይሆናል ብለዋል። መንግሥት ባለፉት ዓመታት በሀገር በቀል እሳቤዎችና ፖሊሲዎች ሀገራዊ አቅሞችን መጠቀም ያስቻሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችንና በርካታ የልማት ኢንሼቲቮችን በመተግበር አስደናቂ እመርታዎች ማስመዝገቡን አንስተዋል። በተለይም በግብርናው ዘርፍ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ላይ የመጣው ለውጥ እና የታየው ስኬት ሊደነቅ የሚገባው ነው ብለዋል። የተለያዩ የግብርና ኢንሼቲቮች የተረጂነትና የጠባቂነት አስተሳሰብን በማስወገድ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆኑንም አንስተዋል። በሌሎች ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶችም እመርታ የተመዘገበባቸውና አመርቂ ውጤት የተገኘባቸው መሆኑን ነው ያወሱት፡፡ በድምሩ ባለፉት ዓመታት በመንግሥት አዳዲስ እሳቤዎችና በሕዝቡ ትብብር በተለያዩ መስኮች የሚታዩና የሚጨበጡ እመርታዎች የተመዘገቡበት መሆኑን ተናግረዋል። የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈጻሚ እና የኦሮሚያ ክልል አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ ተሰማ በበኩላቸው ÷ በመንግሥት ሀገር በቀልና አዳዲስ እሳቤዎች በመታገዝ ባለፉት ጥቂት ዓመታት አስደናቂ ውጤት መመዝገቡን ተመልክተናል ብለዋል። የውጭ ምንዛሪ እጥረትንና የዋጋ ግሽበትን በመቋቋም ጭምር የሀገሪቱን ገጽታ የቀየሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በጥራት እና በፍጥነት በመፈጸም የላቀ እመርታ መታየቱንም አንስተዋል። በጥናት ላይ ተመስርቶ በሀገሪቱ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ መደረጉ ለዜጎች ሰፊ የስራ እድልን ከመፍጠር ባለፈ የውጭ ምንዛሪ ወጪን በመቀነስ ረገድ ትርጉም ያለው ስራ መከወኑን ለኢዜአ አብራርተዋል፡፡ በአዲሱ ዓመት መባቻ ላይ የጳጉሜን ቀናት በተለያዩ ስያሜዎች መከበራቸው በጎ ሀሳቦችን እንድናፈልቅ ልዩ ስሜት እንዲፈጠርብን ያደርጋል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተባባሪ ወይዘሮ ሠናይት በላይ ናቸው፡፡ መንግሥት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር በተለይም በመስኖ ስንዴን በማልማት ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉ ትልቅ እመርታ መሆኑን ገልጸዋል። በቱሪዝም፣ ዲጂታላይዜሽን፣ የአረንጓዴ አሻራ ልማት፣ በአትክልትና ፍሬፍሬ ልማት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች እመርታ መመዝገቡን ማየት ችለናል ብለዋል።