አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም ሁለንተናዊ የኢንተርኔት ተደራሽነትን ይበልጥ በማጠናከር ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው፡፡
ለዚህም ኢትዮ ቴሌኮም የ4ጂ እና 5ጂ ኔትወርክ አገልግሎትን በማስፋፋት ረገድ እያከናወናቸው የሚገኙ ዘርፈ ብዙ ተግባራት የሚደነቁ ናቸው፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በቅርቡ የተቋሙን የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት÷ ኢትዮ ቴሌኮም ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት በማቅረብ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ነው ፡፡
በበጀት አመቱ አዳዲስ የኔትወርክ ጣቢያዎችን ከመገንባት ጎን ለጎን፣ የኔትወርክ አቅምን፣ ሽፋንን እና የተጠቃሚዎችን ተሞክሮ ለማሻሻል የሚያስችሉ መጠነ ሰፊ የ4ጂ እና 5ጂ ኔትወርክ ማሻሻያና ማስፋፊያ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
ተቋሙ በመጠነ ሰፊ የ4ጂ ኔትወርክ ማሻሻያ እና ማስፋፊያ ሥራዎች የ4ጂ የሕዝብ ቁጥር ሽፋንን 82 ነጥብ 23 በመቶ መድረሱን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አመልክተዋል፡፡
በዚህም በዓመቱ 264 አዳዲስ ከተሞች የ4ጂ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን÷ ይህም አጠቃላይ የ4ጂ ሽፋን ያላቸውን ከተሞች ቁጥር ወደ 1 ሺ 200 አድርሶታል።
የ4ጂ የሕዝብ ቁጥር ሽፋን ከ70 ነጥብ 83 ከመቶ ወደ 82 ነጥብ 23 በመቶ እንዲሁም የጂኦግራፊያዊ ሽፋን ከ21 ነጥብ 06 ከመቶ ወደ 36 ነጥብ 29 በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡
የ5ጂ ኔትወርክ ማስፋፊያ ለዘመናዊ ከተሞች ግንባታ (ስማርት ሲቲ)፣ ለኢ-ኮሜርስ፣ ለዲጂታል መንግሥታዊ አገልግሎቶች እና ለፊንቴክ መድረኮች አዳዲስ ዕድሎችን ፈጥሯል፡፡
የ5ጂ ማስፋፊያ ሥራው ተጨማሪ ሰባት ከተሞችን በማካተት በአጠቃላይ በ33 ከተሞች ተደራሽ ማድረግ የተቻለ ሲሆን÷ በበጀት ዓመቱ በተገነቡ 25 አዳዲስ የ5ጂ ጣቢያዎች አማካኝነት ጠቅላላ የጣቢያዎቹ ቁጥር 340 ደርሷል።
ይህም የ5ጂ የመሸከም አቅምን ወደ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን አሳድጓል፤ የተፈጠረው ተጨማሪ የ80 ነጥብ 9 ሺህ አቅም ለዘመናዊ ከተሞች ግንባታ፣ ለኢንተርፕራይዝ ደረጃ አገልግሎቶች እና ለፈጠራ ሥነ ምህዳር ግንባታ ትልቅ አቅም ፈጥሯል፡፡
እነዚህ ጥረቶች አስተማማኝ ሀገር አቀፍ ትስስርን በማረጋገጥ፣ ዲጂታል አገልግሎቶችን በማብቃት እና ኢትዮ ቴሌኮምን በሀገሪቱ የዲጂታል ጉዞ ውስጥ የፈጠራና የተወዳዳሪነት ዋነኛ ሞተር በማድረግ የ”ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030″ ራዕይን ዕውን የሚያደርጉ ናቸው።