አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እውቁ የነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ አንድ ዝነኛ አባባል አላላቸው። ሕዝባቸውን ነፃ ለማውጣት ባደረጉት ንቅናቄ ሕዝቡ ራሱን ካልቻለ፣ ኑሮውን ካላሻሻለ ነፃነቱ ምሉዕ እንደማይሆን አጽንኦት ይሰጣሉ።
«ባዶ ሆድ ነፃነት አይደለም። ድህነት ባለበት እውነተኛ ዴሞክራሲና ሉዓላዊነት ሊኖር አይችልም፤ ዜጎች ከረሃብና ከድህነት ሲላቀቁ ብቻ ነው ሀገራዊ ነፃነታቸው ሙሉ የሚሆነው።» ነው የሚለው የኔልሰን ማንዴላ አባባል።
በዘመናዊው ዓለም የሉዓላዊነትና ነፃነት ትርጉሙ እየተቀየረ ነው። ድህነትን ይዞ ነፃ ሀገርነት የማይሆን ሆኗል። ሉዓላዊነት ከድንበር ባለፈ የፖለሲ ነፃነት ጉዳይ ነው ዛሬ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ጳጉሜ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ባስተላለፉት መልዕክት፣ «አባቶቻችን የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በደምና በአጥንታቸው አስከብረው ታላቅ ሀገር አውርሰውናል፤ ዛሬ ደግሞ እውነተኛ ሉዓላዊነትን እያረጋገጥን ያለነው ከልመናና ከጥገኝነት በተላቀቀው አዲሱና ታሪካዊው መንገዳችን ነው!» ብለዋል።
ሉዓላዊነትን ከወታደራዊ ኃይል ብቻ ያለፈ፣ በምግብ ራስን መቻልና በኢኮኖሚ ጽናት የሚለካ ሀገራዊ እሴት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው የጠቀሷቸውን ሦስት ዋና ዋና ማሳያዎች የስንዴ ምርታማነት፣ የሌማት ትሩፋትና የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄዎች እንዲሁም የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ውሳኔዎችንና ከነሱ ጀርባ ያለውን ተጨባጭ መረጃ እንመልከት።
የዛሬው ትውልድ የአባቶቹን ታሪካዊ አደራ የሚወጣው ሀገርን ከውጭ ወረራ ብቻ ሳይሆን ከድህነትና ከጥገኝነት በመገላገል ጭምር ነው።
ይህ አገላለጽ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የፖሊሲ ንግግር ውስጥ ጎልቶ የሚደመጥ ጭብጥ ነው፤ ሉዓላዊነት ማለት ድንበርን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ ሀገራዊ ውሳኔዎችን ያለ ውጭ ጫና በራስ አቅም መወሰን መቻልንም ያካትታል። ለዚህ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ራስን መቻል ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ ተደርጎ ይወሰዳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) «በሚሊየን በሚቆጠር ዶላር ስንዴ ከማስገባት ተነስተን ዛሬ የአፍሪካ ቀዳሚ ስንዴ አምራች በመሆን የሚሊየን ዶላሮችን ወጪ ማስቀረት ችለናል» ብለዋል።
በ2015 ዓ.ም ብቻ 151 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ተመርቷል። ከዚህ ውስጥም 104 ሚሊየን ኩንታሉ ከመኸር ወቅት፣ 47 ሚሊየን ኩንታሉ ደግሞ ከመስኖ ልማት ተገኘቷል። ይህ የስንዴ ምርት በ2016 ዓ.ም ደግሞ ምርቱ ወደ 23 ሚሊየን ቶን ከፍ እንዳለ ተነግሯል።
በዚያው ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በባሌ ዞን የመጀመሪያውን ብሔራዊ የስንዴ ወጪ ንግድ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በይፋ ያካሄዱ ሲሆን÷ ኬንያና ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ስንዴ ለመግዛት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ይህ ስኬት በዋናነት በመስኖ ልማት መስፋፋት፣ በክላስተር እርሻ አሠራርና በግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችና በብርቱ አርሶ አደሮች ብርቱ ጥረት የሆነ የእመርታ መንገድ ነው።
ለምግብ ሉዓላዊነት የተደረገው ጥረት ግን ይህ ብቻ አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ «በ«ሌማት ትሩፋት» የምግብ ዋስትናን በተግባር እያረጋገጥን፣ በ«ኢትዮጵያ ታምርት» ንቅናቄም አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋትና የስራ ዕድል በመፍጠር ሉዓላዊነታችንን እያረጋገጥን እንገኛለን» ብለዋል።
«ሌማት ትሩፋት» የቤተሰብ ደረጃ የምግብ ራስን መቻል መርሐ ግብር ሲሆን÷ የወተት፣ የእንቁላል፣ የማርና የአትክልት ምርትን በጓሮ አትክልትና በአነስተኛ የቤት እንስሳት እርባታ ደረጃ ለማሳደግ ያለመ ነው።
«ኢትዮጵያ ታምርት» ደግሞ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን በማጠናከር የሀገር ውስጥ ምርትን በውጭ ምርት ምትክ ለማስፋፋት እና ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ያለመ ብሔራዊ ንቅናቄ ነው። እነዚህ ሁለት ንቅናቄዎች ተደጋግፈው፣ ከቤተሰብ እስከ ፋብሪካ ደረጃ ያለውን የምግብና የምርት ሰንሰለት በሀገር ውስጥ አቅም ለመሸፈን ያለመ ስትራቴጂ አካል ናቸው።
ከዚህ ባሻገር የመንግሥት ገቢ አሰባሰብ ሥርዓት ዘመናዊ በማድረግ፣ የፋይናንስ ዘርፍን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት በማድረግ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲጨምር የተደረጉ ርምጃዎች የዚሁ ሪፎርም አካል ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ «እነዚህ ሁሉ ታላላቅ ድሎች ኢትዮጵያ በሚያጋጥሟት ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ሸብረክ ሳትል በጽናት መጓዝ መቻሏን የሚያረጋግጡ ህያው ምስክሮች ናቸው፤ ይህ የእመርታ ጉዟችን ለመጪው ዓመት የሰነቀው ተስፋ እጅግ ግዙፍ ነው!» ብለዋል።
ይህ የጳጉሜ መልዕክት ከሀገራዊ ማንነትና ከታሪካዊ አደራ ጋር የተሳሰረ ሲሆን፣ የግብርና፣ የኢንዱስትሪና የማክሮ-ኢኮኖሚ ስኬቶችን በአንድ ወጥ ትርክት ያስቀመጠና የኢትዮጵያን ማንሰራራት አይቀሬነት ያሳየ ነው።
በአፈወርቅ እያዩ