የሀገር ውስጥ ዜና

በፕሬዚዳንት ታዬ የተመራ ከፍተኛ የመንግሥት ልዑክ ዱባይ ገባ

By amele Demisew

September 06, 2026

 

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የተመራ ከፍተኛ የመንግሥት ልዑክ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ማምሻውን ዱባይ ገብቷል።

በፕሬዚዳንት ታዬ የተመራው ልዑክ ዱባይ ሲደርስ በሀገሪቷ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

የኢንቨስትመንት ጉባዔው ከነገ ጳጉሜን 2 ጀምሮ እስከ 4 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ቀናት በዱባይ ዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከል ይካሄዳል።

በየዓመቱ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባዔ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋት በሀገራት መካከል አጋርነትና የኢከኖሚ ትብብርን ያጠናክራል፡፡

በተጨማሪም በመስኩ የሚስተዋሉ ችግሮችን እልባት በመስጠት በመካከለኛው ምስራቅ ዋነኛ የኢንቨስትመንት መድረክም ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡

በጉባኤው የሀገራት መሪዎች፣ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ ግዙፍ የቢዝነስና ተቋማት ሥራ አስፈጻሚዎች፣ፖሊሲ አውጪዎች፣ ሥራ ፈጣሪዎች፣ የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት ተወካዮች፣ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት በመድረኩ በጋራ ይመክሩበታል።