የሀገር ውስጥ ዜና

የኃይል አብዮት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ማንሠራራት

By Melaku Gedif

September 07, 2026

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ዕድገትና የኢንዱስትሪ ሽግግር እንዲሁም ሁለንተናዊ ብልጽግና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

ኢትዮጵያም በተለያዩ ዘርፎች የጀመረችው የማንሠራራት ጉዞ እውን ሊሆን የሚችለውም አስተማማኝ እና ዘላቂ የኃይል መሠረተ ልማት ሲኖር ብቻ ነው።

“የኢትዮጵያ ሕዳሴ ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል ማሰብ አይቻልም። የኃይል አቅርቦት የኢንዱስትሪ፣ የግብርና እና የቴክኖሎጂ ሽግግራችን የጀርባ አጥንት ነው። እኛ ኃይል የምናመነጨው ለራሳችን ብርሃን ብቻ ሳይሆን የቀጣናውን ሀገራት በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር እና አፍሪካዊ እህትማማችነትን በጋራ ልማት ለማጠናከር ነው፤” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመጀመሪያውን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተርባይን ኤሌክትሪክ ማመንጨት ሥራ ያስጀመሩበት ወቅት የተናገሩት ነው።

የእርሳቸው ንግግር ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግና ኃይል ምን ያህል መሠረት እንደሆነ የሚያሳይ ነው። የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ጥንካሬ እና የሕዝቦች ብልጽግና የሚለካው ባለው የኃይል አቅርቦት ልክ ነው።

በመሆኑም ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ማልማት የሀገሪቱ የኢንዱስትሪ፣ የቴክኖሎጂ እና የከተማነት ሽግግር ዋና ሞተር ሆኖ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ባለፉት ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ላይ በተከናወነው ሰፊ ሥራ፣ የሀገሪቱ የኃይል የማመንጨት አቅም ከነበረበት 4 ሺህ 462 ሜጋ ዋት ተነሥቶ ከእጥፍ በላይ በማደግ ከ9 ሺህ 730 ሜጋ ዋት በላይ ደርሷል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የምታመነጨው ኃይል ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ ከአካባቢ ብክለት ነፃ ከሆኑ ታዳሽ ምንጮች የሚገኝ ነው። እነርሱም የውሃ ኃይል፣ የንፋስ ኃይል፣ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል፣የፀሐይ ኃይል እና የጂኦተርማል ኃይል ናቸው።

ለዚህ ታሪካዊ የማንሠራራት ጉዞ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በከፊል ወደ ሥራ መግባቱ ነው።

ግድቡ በሁሉም ተርባይኖቹ ሙሉ በሙሉ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር ከ5 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የማመንጨት አቅም ይኖረዋል።

በተጨማሪም ግንባታው 77 በመቶ ላይ የደረሰው የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ፣ 1 ሺህ 800 ሜጋ ዋት ተጨማሪ ኃይል ወደ ዋናው መስመር ይቀላቅላል።

አስተማማኝና ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ለአምራች ኢንዱስትሪዎች፣ ለኮንስትራክሽን እና ለቴክኖሎጂ ፓርኮች በማቅረብ የሀገር ውስጥ ምርታማነትን ከማሳደጉም በላይ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን እያሳደገ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለሱዳን፣ ጅቡቲ እና ኬንያ ኤሌክትሪክ በመሸጥ ላይ ስትሆን፤ ወደ ታንዛኒያ እና ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የኃይል መስመሮችን በመዘርጋትና ሽያጭ ለመጀመር የተደረጉ ስምምነቶች እየተተገበሩ ይገኛሉ። ይህም ኢትዮጵያን የቀጣናው የኃይል ማዕከል ያደርጋታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) “የመደመር መንገድ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት÷ እውነተኛ ልማትና ዕድገት የሚረጋገጠው በሀገር ውስጥ ብቻ በሚደረግ ጥረት ሳይሆን ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሚፈጠር የጠበቀ የኢኮኖሚ ትስስርና የጋራ ተጠቃሚነት ነው።

የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ደግሞ ድንበር ተሻጋሪ ትስስርን በመፍጠር፣ ቀጣናዊ ውህደትን በማፋጠን እና ሰላምን በመገንባት በኩል የማይተካ ሚና ይጫወታል።

የኃይል አብዮት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ማንሠራራት እና የኢኮኖሚ ሽግግር መሠረት ነው። ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ያላትን እጅግ ከፍተኛ እምቅ አቅም በአግባቡ መጠቀም መቻሏ ሀገሪቱ ከድህነት እንድትወጣ እና ቀጣናዊ የኃይል ማዕከል እንድትሆን ያደርጋታል።

የኃይል አቅርቦት ልማቱ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል፣ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋት እና ኢትዮጵያን የአፍሪካ የታዳሽ ኃይልና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ተመራጭ ማዕከል ለማድረግ እየተከናወነ ያለ የሀገሪቱን የማንሠራራት ጉዞ ያፋጠነ ታሪካዊ ሽግግርም ነው።

በታሪኩ ለገሰ