የሀገር ውስጥ ዜና

የዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ትብብር ለዘላቂ ሰላምና ብልፅግና አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል – አቶ አደም ፋራህ

By Yonas Getnet

September 07, 2026

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ትብብር ለዘላቂ ሰላምና ብልፅግና አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው አሉ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፡፡

ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች (ICDPP) የምክክር መድረክ በደቡብ ኮሪያ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የምክክር መድረኩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብን ፍላጎት የሚያንፀባርቁ መሪዎችን የሚያፈሩና ፖሊሲዎችን የሚቀርፁ መሆናቸውን ታሳቢ ማድረግ አለበት።

መድረኩ በመንግሥታት መደበኛ ዲፕሎማሲና በሕዝቦች መካከል ባለው ግንኙነት መካከል ያለውን ክፍተት የሚሞላ ወሳኝ የጋራ መድረክ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የሃሳብ ብዝኃነት፣ ሉዓላዊ እኩልነት፣ አካታችነት፣ ተቋማዊነትና በተጨባጭ ትብብር መርሆዎች ሊመራ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡

የምክክር መድረኩ በዋናነት ዲሞክራሲያዊና ተቋማዊ ጥንካሬን ለማረጋገጥ፣ አካታች ልማትና ኢኮኖሚያዊ ትራንስፎርሜሽንን ለማምጣት እንዲሁም ግንባታና ቅድመ ግጭት መከላከልን ለማጠናከር ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ብልፅግና ፓርቲ የሚመራበትን የመደመር እሳቤ መሠረት በማድረግ ሁሉንም አቅሞች ተጨማሪ እሴትና አቅም በሚፈጥር አኳኋን በመጠቀምና በማጎልበት የምግብ ሉዓላዊነትን፣ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና ምርታማነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል አስረድተዋል።

መድረኩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መርህን መሰረት ያደረገና በተግባር ላይ ያተኮረ ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ በማስቻል ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት፣ የጋራ ብልፅግና፣ ፍትህና ርትዕ የተረጋገጠበት ዓለም ለመፍጠር አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት እምነታቸው ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የምክክር መድረክ ከእስያ፣ አፍሪካ፣ አሜሪካና አውሮፓ የተወጣጡ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መሪዎችን የሚያገናኝ መሆኑን ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡