አዲስ አበባ፣ጳጉሜን 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ኢትዮጵያ የንጹህ ኃይል ልማቷን በማጠናከር ለጎረቤት ሀገራት የምታቀርበውን የኃይል መጠን ለማሳደግ እየሰራች ነው አሉ።
ዓመታዊው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ጉባኤ (ኤአይኤም ኮንግረስ) በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ዱባይ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ጉባኤው የዓለም ኢኮኖሚ መዋቅር በመሰረታዊነት እየተለወጠና የቴክኖሎጂ ለውጦች አጠቃላይ ሁኔታዎችን እየቀየሩ ባለበት ጊዜ መካሄዱ ጠቃሚ ያደርገዋል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ተለዋዋጭ የጂኦፖለቲካ ሁኔታዎች የዓለምን የንግድ የእሴት ሰንሰለት እየወሰኑ መምጣታቸውን ገልጸው፥ እነዚህ ክስተቶች በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት በተለይም በአፍሪካ ካስከተሉት ችግር ባልተናነሰ ወደ ውስጥ ለመመልከት ዕድል ፈጥረዋል ነው ያሉት።
የአፍሪካ ሀገራት የዚህ ተለዋዋጭ ዓለም ክስተት ተመልካች ሳይሆኑ ዋነኛ ተሳታፊና ሥርዓት ገንቢ አካል እንዲሆኑ በአፍሪካ ኅብረት በኩል የጋራ መግባባት መደረሱን ተናግረዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት እየተገበረቻቸው ያሉት ተከታታይ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ተግባራት በዚህ መንገድ የተቃኙ መሆናቸውን አብራርተዋል።
አፍሪካ ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚ እንድትገነባ ያላትን የስትራቴጂያዊ ኢንቨስትመንት ዕድሎች አሟጥጣ ለመጠቀም አምስት ዋና ዋና ጉዳዮችን ማከናወን ይጠበቅባታል ነው ያሉት።
እንደ ሀይድሮ ኤሌክትሪክ፣ ንፋስ፣ ፀሐይና አንፋሎት ያሉ የንጹህ የኤሌትሪክ ኃይል ልማትን ማስፋፋትና በግብርና ዘርፍ ላይ በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም በስንዴ ምርት ዘርፍ ያስመዘገበችውን እመርታ በተሞክሮነት ያቀረቡ ሲሆን፤ የንጹህ የኃይል አማራጭን ለፈጣን የኢኮኖሚ እድገት መሰረት አድርጋ እንደምትወስድ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከንጹህ ኃይል ብቻ 60 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም እንዳላት ገልጸው፤ በፈረንጆቹ 2030 13 ሺህ ሜጋ ዋት ለማመንጨት ማቀዷን ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም በማዕድን ልማትና በዲጂታል መሰረተ ልማት እንዲሁም በሰው ኃይል ልማት ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ሀገራት ለዘላቂና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት የመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ትኩረት አድርገው መስራት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚሰራውን ሥራ ለአብነት ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋነኛ የትስስር ማዕከልነቷን ለማፅናት የሚያስችላትን የቢሾፍቱ አየር መንገድ በ12 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር እየገነባች ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡