አዲስ አበባ፣ጳጉሜን 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እና ቱርክዬን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በቁርጠኝነት ይሰራል አሉ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ።
በደቡብ ኮሪያ እየተካሄደ በሚገኘው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክክር መድረክ ጎን ለጎን አቶ አደም ፋራህ ከቱርክዬ ፍትሕና ልማት (ኤኬ) ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት ዛፌር ሲራካያ ጋር መክረዋል፡፡
አቶ አደም በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነትን ማጠናከር ለሀገራት ዘርፈ ብዙ ግንኙነት መጠናከር ጉልህ ፋይዳ ያለው በመሆኑ በትኩረት ይሰራል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የቱርክዬ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶኻ በተደጋጋሚ በመምከር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማላቅ የተደረሱ ስምምነቶችን ከግብ ለማድረስ ቀጣይነት ያለው ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ እና በኤኬ ፓርቲ መካከል በፈረንጆቹ 2025 የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ተፈጻሚ እንዲሆን የጋራ መድረኮችን ከማካሄድ ባለፈ ዝርዝር አፈፃፀሙ ላይ ጠንካራ ክትትል የሚያደርግ አካል እንደሚመደብ ጠቁመዋል።
ቱርክዬ በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን ከከፈተች 100 ዓመት መሙላቱን አስታውሰው÷ ይህንን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስና ወደ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ ለመቀየር ብልጽግና ፓርቲ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
ዘመናትን ያስቆጠረው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች በትብብር ለመስራት እድሎችን የፈጠረ መሆኑ በውይይቱ ላይ ተነስቷል።
ይህንን ትብብር በማስፋት በፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት ለማስቀጠል እንዲቻል ብልጽግና ፓርቲ እና ኤኬ ፓርቲ በጋራ ለመስራት በአዲስ አበባ የተፈረመው የሁለትዮሽ ስምምነት አጋዥ እንደሆነ ተገልጿል።
በዋናነትም የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስፋት፣ የሁለትዮሽ ግንኙነትን አጠናክሮ በማስቀጠል እና በአቅም ግንባታ መድረኮች የአመራሮችን አቅም በቀጣይነት እየገነቡ ለመሄድ የታቀዱ ሥራዎች ወደ ተግባር ሊቀየሩ እንደሚገባ በመድረኩ ተመላክቷል፡፡