የሀገር ውስጥ ዜና

ኦሮሚያ ባንክ አባ ፈርዳ ረሚት የተባለ ዲጂታል የሐዋላ መላኪያ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

By tigist gizachew

September 08, 2026

አዲስ አበባ፣ጳጉሜን 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኦሮሚያ ባንክ ከ ካቻ ዲጂታል ፋይናንሻል አግልግሎት ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች አባ ፈርዳ ረሚት የተባለ ዲጂታል የሐዋላ መላኪያ መተግበሪያ ይፋ አድርጓል፡፡

አባ ፈርዳ ረሚት የተሰኘው የዲጂታል ሐዋላ መላኪያ መተግበሪያ የበለጸገው ከካቻ ዲጂታል ፋይናንሻል አግልግሎት ጋር በመተባበር መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

በውጭ ሀገር የሚኖሩ ገንዘብ ላኪዎች የአባ ፈርዳ ረሚት መተግበሪያን ከአፕስቶር ወይም ከጎግል ፕሌይ በማውረድ መጠቀም እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ደንበኞች መተግበሪያውን በመጠቀም እንደ የትምህርት ቤት ክፍያ፣ የሕክምና ወጪ እና የመኖሪያ ቤት ክፍያ ለመሳሰሉ የተረጋገጡ መሰረታዊ ወጪዎች መላክ እንደሚችሉ ተመላክቷል፡፡

የአባ ፈርዳ ረሚት መተግበሪያን ደንበኞች ሲጠቀሙ የሚላከው ገንዘብ በቀጥታ አስቀድመው ይጠቀሙባቸው ከነበሩ ማንኛውም የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ የባንክ ሒሳቦች ጋር አስተሳስረው መጠቀም የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።

የገንዘብ ልውውጥ ደህንነትን በተመለከተ መተግበሪያው የላቀ የኢንክሪፕሽን ሥርዓትን መጠቀሙ ነው የተገለጸው፡፡

በዚህም ክፍያ ተቀባዩ ተቋም እና የካርድ መረቡ የካርድ ባለቤቱን ማንነት በጥብቅ በማረጋገጥ በከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚፈጸም ተጠቁሟል፡፡

መተግበሪያው ይፋ ሲደረግ የሁለቱም ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በአብረሃም አበራ