አዲስ አበባ፣ጳጉሜን 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማንኛውም ማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ በማድረግ አለኝታችንን ልናሳይ ይገባል አሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፡፡
አፈ ጉባኤ አገኘሁ የ2019 ዘመን መለወጫ አዲስ ዓመትን አስመልክቶ በምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ለሚገኙና ዝቅተኛ የወር ገቢ ላላቸው ሰራተኞች ድጋፍ አድርገዋል፡፡
አቶ አገኘሁ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ድጋፍ ማድረግ ግለሰባዊ፣ ተቋማዊ እንዲሁም ሀገራዊ ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመው፣ አንዱ ለሌላው አጋርነቱን በተግባር ሊያሳይ ይገባል፡፡
ለፌደሬሽን ምክር ቤት ሰራተኞች የተደረገው ድጋፍ ተቋሙ በማንኛውም ማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው እና ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ በማድረግ የወገን አለኝታነቱን ለማሳየት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ድጋፍ የሚያደርገው የተሻለ አቅም ያለው እና የተረፈው ብቻ አይደለም ያሉት አፈ ጉባኤው ÷ ማህበረሰቡ ካለው ላይ ቀንሶ አቅመ ደካሞችን ሊደግፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በመጪው አዲስ ዓመት በሚከበሩ በዓላት የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህልን በማጠናከር አቅመ ደካሞችን መርዳት እና ማህበራዊ ትስስርን ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
መጪው አዲስ አመት የሰላም፣ የልማት እና የብልጽግና እንዲሆን መልዕክት ማስተላለፋቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡