የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ጀምሮ የአፍሪካ ድምጽ መሆን ችላለች – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Mikias Ayele

September 09, 2026

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የአፍሪካ ድምጽ መሆን ችላለች አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) 24ኛውን የአፍሪካ ሕብረት ቀን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ÷ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጀምሮ እስከ አፍሪካ ህብረት ድረስ ባለው ጉዞ የአፍሪካ ድምጽ ሆና መቆየቷን አስታውሰዋል፡፡

አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በመሆን ስታገለግል ቆይታለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ ለወደፊትም የኢትዮጵያ አህጉራዊ መሪነት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተቀናጀች እና የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የተቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደምትሰራ አረጋግጠዋል፡፡

በአፍሪካ ህብረት የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የዲጂታል ጤና ሻምፒዮን ሆነው መሰየማቸውን ጠቁመው ÷ የአፍሪካ መሪዎችና ወጣቶች የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትን እንዲያረጋግጡ እና የአፍሪካን የዲጂታል ዕጣ ፋንታ በራሳቸው እንዲቀርፁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር በትብብር በመሆን የአፍሪካን መጻኢ እድል በጋራ ለመወሰን ሁሌም ቁርጠኛ ናት ሲሉም ገልጸዋል፡፡