የሀገር ውስጥ ዜና

ተረጅነትን ታሪክ ያደረገው የግብርናው ዘርፍ አስደናቂ ጉዞ

By tigist gizachew

September 09, 2026

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከታደለችው የተፈጥሮ ሃብት በመነሳት የምግብ ጥገኝነትንና ተረጅነትን ለማስቀረት አበረታች የግብርና ልማት ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች፡፡

የምግብ ሉዓላዊነት ማለት የኢኮኖሚ ነጻነት እና የሀገር ክብር ማረጋገጫ ነው፡፡ መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት ዘርፉን የኢኮኖሚው ምሰሶ አድርጎ መቅረጹ ለግብርናው ዕድገት ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

ግብርናው ከባሕላዊ አሠራር ወጥቶ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ፣ ትራክተሮች፣ ኮምባይነሮች እና የውሃ ፓምፖችን በስፋት ለአርሶ አደሮች እንዲደርሱ ተደርጓል፡፡ ወንዞችን፣ ጥልቅ ጉድጓዶችን እና አነስተኛ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በዓመት ሁለት እና ሦስት ጊዜ ማምረት እንደሚቻል በተግባር ታይቷል፡፡

በዚህ ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ተጨባጭ ለውጥ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ እና የተረጅነት ታሪክን የመቀየር ግስጋሴዋን እንድታስቀጥል አስችሏታል፡፡ በበጋ ስንዴ ልማት እና በመስኖ ሥራዎች የታየው ለውጥ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ምግብ መሸፈን እንደምትችል ማሳያ ሆኗል።

ይህ ስር ነቀል ለውጥ የመጣው በዘፈቀደ ሳይሆን፤ በተቀረጹ ስትራቴጂካዊ ፖሊሲዎች፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በሰብል ብዝሃነት በተከናወኑ ተግባራት በመደመር መንግስት ጽናት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ፣ ለጎረቤት ሀገራት መላክ መጀመሯ ታሪካዊ ስኬት ነው፡

የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጉዞ የጠንካራ ፖሊሲ፣ የሰላም፣ የታታሪነት እና የዓለም አቀፍ አጋርነት ውህደትን አጥብቆ የሚሻ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የስንዴና የግብርና ሉዓላዊነት ጉዞ ካስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባሻገር፣ ትልቁ ስኬቱ በዜጎች ህሊና ውስጥ የፈጠረው ጥልቅ የስነ ልቦና ስብራት ጥገና ነው።

ይህ የግብርና ሽግግር ኢትዮጵያ የምግብ ነጻነቷን አውጃ ወደ ብልጽግና የምታደርገውን የማይቀለበስ ጉዞ የሚያሳይ ህያው ምስክር ነው።

የኢትዮጵያ ከተረጅነት ወደ ምግብ ሉዓላዊነት የምታደርገው ጉዞ፣ ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ የተቀናጀ የህዝብ ተሳትፎ እና የሀገር ውስጥ አቅምን መጠቀም ከተቻለ የትኛውንም የኢኮኖሚ ታሪክ መቀየር እንደሚቻል ማረጋገጫ ነው፡፡

ይህ ጉዞ ህዝብን ከመመገብ ባለፈ፤ የሀገርን ክብርና የኢኮኖሚ ነጻነት በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ከፍ የሚያደርግ የማይቀለበስ መስመር ነው፡፡

በትዕግስት ግዛቸው